ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ አስመልክቶ ዛሬ በሰጠው መግለጫ፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ለኢትዮጰያ ሕዝብ ባስተላለፈው መልዕክት ለስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ እንኳን በሰላም አደረሳችሁ በማለት፣ “የምርጫው ሂደት ተጀምሮ አሁን ያለበት ደረጃ እስኪደርስ በጨዋነትና በትዕግስት ላደረጋችሁት ድጋፍ እና ትብብር የላቀ ምስጋናውን እያቀረበ፤ በቀሪው የምርጫ ሂደትም ምርጫውን የሚያደናቅፍ አጠራጣሪ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ እንደተለመደው ኹሉ መረጃ በመስጠትና አስፈላጊውን ድጋፍ ለጸጥታ እና ደኅንነት ኃይሉ በማድረግ የበኩላችሁን ድርሻ እንድትወጡ ጥሪውን ያቀርባል” ብሏል፡፡
በተጨማሪም ለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባስተላለፈው መልዕክቱ “የምርጫ ሕጉንና የሥነ ምግባር ደንቡን አክብራችሁ እስከ አሁን ለምርጫው ሰላማዊነት የበኩላችሁን ገንቢ አስተዋጾኦ በማበርከታችሁ ኮሚሽኑ ምስጋናውን እያቀረበ፣ በቀጣይም በሚኖረው የምርጫ ሂደት እስከመጨረሻው ሰላማዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ ሀገራዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ ኮሚሽኑ በጥብቅ ይጠይቃል” ሲል አሳስቧል፡፡
ኮሚሽኑ ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ወሳኝ ምዕራፍ ከግምት ውስጥ በማስገባት የምርጫ ሂደቶች ከሁከትና ብጥብጥ የፀዱ እንዲሆኑ ከፀጥታና ደኅንነት መዋቅር ጋር የተቀናጀ የምርጫ ደኅንነት እቅድ በማዘጋጀት በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ዕለት እና በድህረ ምርጫ ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ውስጣዊ እና ውጫዊ የጸጥታ ሁኔታዎችን በአግባቡ በመተንተን እና በመለየት አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ሲሠራ መቆየቱን ያወሳው ፖሊስ “መላው ሕዝብ እና የጸጥታ ሀይል ከመቼውም ጊዜ በላይ በመቀናጀት ይህን ታሪካዊ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ እንዲወጣ ጥሪውን በከፍተኛ አክብሮት እያቀረበ በድምጽ መስጫ ዕለትና በድህረምርጫ ወቅት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ኹሉ በሕግ አግባብ ብቻ እንዲሆኑ ኮሚሽኑ በጥብቅ ያሳውቃል” ሲልም መልዕክቱን አስተላልፏል።