ምርጫ ጣቢያ ውስጥ “ምጥ” የጀመራቸው ሁለት እናቶች በሰላም ተገላገሉ!

ምርጫ ጣቢያ ውስጥ “ምጥ” የጀመራቸው ሁለት እናቶች በሰላም ተገላገሉ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– አንደኛዋ እናት፣ ወይዘሮ ውባየሁ ወርቁ ይባላሉ፡፡ ነዋሪነታቸው በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ጓንጓ ወረዳ ነው፡፡ እርሳቸው የሚኖሩባት ቀበሌ ደግሞ ሉንፅ ደገራ ትባላለች፡፡ ወይዘሮ ውባየሁ ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫን ለመምረጥ ወደምርጫ ጣቢያ ሄዱ፡፡ በምርጫ ጣቢያው ሳሉ ያልጠበቁት ነገር ተሰማቸው፡፡ የምጥ ምልክትም ታያቸው፡፡

ከወረፋ ቀድመው ይመርጡ ዘንድ ዕድል ተሰጣቸው፡፡ ምጡ ጠበቀ፡፡ በስፍራው የነበሩ አስታባባሪዎች ወደጤና ጣቢያ ይሄዱ ዘንድ አመቻቹ፡፡ ለአምቡላንስ ተደወለና ወደ ሆስፒታል ይዛቸው ከነፈች፡፡ ቻግኒ ሆስፒታል እንደደረሱ ሴት ልጅ በሰላም ተገላገሉ። መረጃውን ያደረሰን የጓንጓ ወረዳ ኮምዩኒኬሽን ጽ/ቤት እንደገለጸው፣ ወይዘሮ ውባየሁ በዚህ ታሪካዊ ቀን፣ ፈጣሪያቸውን በማመስገን ልጃቸውን በፍቅር ለማቀፍ በቅተዋል።

አበራሽ ጉታ የተባሉት ሁለተኛዋ እናትም፣ በአርሲ ዞን ሄጦሳ ወረዳ ድምፅ ለመስጠት በሄዱበት ምጥ ጀምሯቸው ድምጽ ከሰጡ በኋላ በሰላም ተገላግለዋል፡፡

ወ/ሮ አበራሽ ድምፅ ለመስጠት በሄዱበት ሄጦሳ ዙሪያ ምርጫ ጣቢያ ውስጥ ምጥ ሲጀምራቸው እንደምንም ድምፅ ከሰጡ በኋላ ወደ ህክምና ተቋሞ በማቅናት ወንድ ልጅ ተገላግለዋል፡፡ ለልጃቸው “ታሪኩ” የሚል ስያሜ እንደሰጡትም የሄጦሳ ወረዳ ኮሙኒኬሽን ዘግቧል፡፡

LEAVE A REPLY