ዛሬ 207 የምርጫ ችግሮች መፈጠራቸውን ኢዜማ አስታወቀ!

ዛሬ 207 የምርጫ ችግሮች መፈጠራቸውን ኢዜማ አስታወቀ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በምርጫ 2013 የድምጽ መስጫ ቀን ያጋጠሙ እና በቀሩት ሰዓታት አፋጣኝ መፍትሄ የሚገባቸው ባላቸው ጉዳይ ላይ፣ ዛሬ ከቀኑ 10፡00 ሰዓት በዋና ጽሕፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ከመላ ሀገሪቱ የደረሱትን ሪፖርቶች መሰረት አድርጎ 207 ችግሮች መፈጠራቸውን አስታውቋል።

የኢዜማ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ “ያጋጠሙ ሶስት ዋና ዋና በአዲስ አበባ ጉዳዮች” በሚል በሰጡት አጭር መግለጫ “በአማራና በደቡብ ክልል አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች የኢዜማ ታዛቢዎች እንዳይገቡ ተከልክለዋል። ከገቡ በኃላ የተባረሩ እንዲሁም ምርጫው አልቋል በሚል የተባረሩም አሉ። በአዲስ አበባ አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎችም የምርጫ ቁሳቁስ ምርጫ በሰዓቱ ባለመድረሱ መራጮች ከሶስትና አራት ሰዓታት በላይ ፀሀይ ላይ ተሰልፈው እንዲሰላቹና ተስፋ እንዲቆርጡ ተደርጓል። ካድሬዎች በሰልፍ መሀል እየገቡ ቅስቀሳ ማድረጋቸውም ተስተውሏል” ሲሉ ገልፀው፣ ችግሮቹን ወዲያውኑ ለምርጫ ቦርድና ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ማሳወቃቸውንና ዘግይቶ በተጀመረባቸው ጣቢያዎችም የሰዓት ማሻሻያ እንዲደረግ መጠየቃቸውን አመልክተዋል።

የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ሀላፊ አቶ ዋስይሁን ተስፋዬ በበኩላቸው፣ ጋዜጣዊ መግለጫውን ለመስጠት የተፈለገው፣ ችግሮቹ በጊዜ መፈታት ካልቻሉ በአጠቃላይ የምርጫ ውጤቱ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ስለሚኖራቸው መሆኑን ጠቁመው “እስካሁን ባለን መረጃ አዲስ አበባን ሳይጨምር ከመላ ሀገሪቱ 207 ችግሮች ተፈጥረዋል” ብለዋል።

ለፓርቲው ከደረሱ መረጃዎች መካከል የተወሰኑትን የጠቀሱት አቶ ዋስይሁን “ለምሳሌ ያክል፤ በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን ኦፋ ምርጫ ጣቢያ ታዛቢዎቻችን ሳይገኙ በፊት ምርጫው እንዲጀመር ተደርጓል። በቦሊሶ ሶሬ እና በመስቃን ማረቆ ታዛቢዎቻችን ተባረዋል። በሃዲያ ሶሮ 01 ኮሮጆ መሰበር አጋጥሟል። በምዕራብ ጎጃም አማኑኤል ምርጫ ወረዳ የወረዳው ግብርና ሃላፊ፣ በሉማሜ የወረዳው ሊቀመንበር የሚስጥር ድምጽ መስጫ ውስጥ ተቀምጠው መራጮችን ነጻነት ሲያሳጡ ውለዋል። በደቡብ ጎንደር ፋርጣ 1 ላይ የታጠቁ ሚሊሻዎች ምርጫ ጣቢያ ውስጥ ገብተው ህዝቡን እያስፈራሩ እንደዋሉ መረጃ ደርሶናል። እንደዚሁም በጋምቤላ ላሬ ምርጫ ጣቢያ፣ በሰሜን ሸዋ ሁለት ምርጫ ጣቢያዎችና በአሶሳ፣ ሀዋሳን ጨምሮ በአንዳንድ የሲዳማ ምርጫ ጣቢያዎች ምርጫው አልቋል ተብሎ ቆጠራ ተጀምሯል። በአዳማ አንዳንድ ምርጫ ጣቢያዎችም ድምጽ መስጫ ወረቀት አልቋል ተብሎ ምርጫው ቆሟል” በማለት አስታውቀዋል።

LEAVE A REPLY