ምርጫውን ለመታዘብ የመጣው አሜሪካዊ በሆቴል ክፍሉ ውስጥ ሞቶ ተገኘ!

ምርጫውን ለመታዘብ የመጣው አሜሪካዊ በሆቴል ክፍሉ ውስጥ ሞቶ ተገኘ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በካርተር ማዕከል ተወክሎ 6ኛውን አገራዊ ምርጫ ለመታዘብ ወደኢትዮጵያ የመጣው አሜሪካዊ፣ በአዲስ አበባ ራዲሰን ብሉ ሆቴል መኝታ ክፍሉ ውስጥ ህይወቱ አልፎ መገኘቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።

የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ “ትናንት በራዲሰን ብሉ ሆቴል አሜሪካዊ ዜጋ በመኝታ ክፍሉ ሕይወቱ አልፎ ተገኝቷል” በማለት የሆቴሉ የጽዳት ሠራተኛ ትናንት ጠዋት አንድ ሠዓት ገደማ አሜሪካዊው ያረፈበትን የመኝታ ክፍል ለማጽዳት ስትገባ ያየችውን ነገር ለፖሊስ ጥቆማ መስጠቷን ገልጸዋል።

ፖሊስ መረጃውን እንዳገኘ ወደ ስፍራው መንቀሳቀሱንና አሜሪካዊው ከአልጋው ላይ ወደ መሬት ወድቆ ሕይወቱ አልፎ መገኘቱን ያመለከቱት ኮማንደር ፋሲካ፣ በሟች ኪስ ውስጥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ልዩ የምርጫ ታዛቢ ወረቀት (ባጅ)፣ የተለያዩ መታወቂያዎችና መንጃ ፈቃድ መገኘታቸውን ገልጸው፣ መንጃ ፈቃዱ “በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ብሔራዊ የድራይቪንግ ላይሰንስ” የሚል እንደሆነም አስረድተዋል።

“አሜሪካዊው የሚጠቀምባቸው በርካታ መድሃኒቶችን ፖሊስ አግኝቷል። ምናልባት ሁኔታው ሲታይ በተፈጥሮ የሞተ ይመስላል። ነገር ግን ትክክለኛው መረጃ ከአስከሬን ምርመራ ውጤት በኋላ የሚታወቅ ነው” ያሉት ዳይሬክተሩ “በአሜሪካዊው ዜጋ ሰውነት ላይ ምንም አይነት የአካል ጉዳትና ቁስለት አልተገኘም። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንና በአዲስ አበባ ከሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ጋር በመሆን በአሜሪካዊው ዜጋ አሟሟት ላይ ምርምራ እያደረጉ ነው። ፖሊስ አጠቃላይ የምርመራውን ውጤት በቀጣይ ይፋ ያደርጋል” ሲሉም ገልጸዋል።

LEAVE A REPLY