ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ለስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ሽፋን እየሰጡ ከሚገኙ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን መካከል አንዱ የሆነው ሲኤን ኤን (CNN)፣ ምርጫው ከ16 ዓመታት በኋላ በርካታ ፓርቲዎች የሚሳተፉበት የመጀመሪያው ምርጫ እንደሆነ ዘግቧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የ2019 የዓለም የሰላም ኖቤል ሽልማት አሸናፊ መሆናቸውን ያስታወሰው ሲኤን ኤን፣ “ፓርቲያቸው ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛውን ድምፅ ካሸነፈ እርሳቸው በድጋሚ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሆኑ ይጠበቃል” ብሏል።
አልጀዚራ በበኩሉ፣ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች “ምርጫው ለኢትዮጵያ ወሳኝ ነው” ማለታቸው የተገለፀ ሲሆን፣ ተመራጩ መንግስት ሰላምን እና አንድነትን ያመጣልናል ብለው ተስፋ ማድረጋቸው በዘገባው ጠቁሟል፡፡
አብላጫ ድምፅ ያገኘው ፓርቲ በቀጣይ መንግስት የሚመሰርት መሆኑን ያመለከተው አልጀዚራ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ “ምርጫው ነፃ እና ፍትሃዊ ይሆናል” ማለታቸውንም አውስቷል።
ዘጋርዲያን ደግሞ፣ የኢትዮጵያን ምርጫ አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ “መላው ዓለም በምርጫው ቀን እርስ በእርስ ይጋጫሉ ብሎ ሲጠብቅ እኛ ግን የተለየ ነገር እናሳያቸዋለን፡፡ ኢትዮጵያን ከመበታተን የጠበቃት ኃይል ነገ የአፍሪካን ቀንድ የአፍሪካ ክንድ ያደርጋታል” በሚል በጅማ ስታዲየም ተገኝተው ያደረጉትን ንግግር በማስታወስ ዘገባውን ጀምሯል፡፡
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ምርጫዎች ሁሉ በተለየ ሁኔታ በርካታ እጩዎች እየተወዳደሩ ናቸው ማለቱንና ከ37 ሚሊየን በላይ ኢትዮጵያውያን ለመምረጥ መመዝገባቸውን የጠቀሰው የዘጋርዲያን ዘገባ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ተዘዋውሮ ካነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ሚሊዮን ገብረእግዚአብሔር የተባሉ ግለሰብ “ይሄ ምርጫ የተለየ ነው፤ አወዳድረን ልንመርጥ የምንችላቸው በርካታ ፓርቲዎች አሉ፡፡ ከዚህ ቀደም አንድ ፓርቲ ብቻውን ይወዳደር ስለነበር እንዲህ ያለ ዕድል አልነበረንም” ማለታቸውንና
ዮርዳኖስ ብርሃኑ የተባለ የ26 አመት ወጣትም “ምርጫው የአገሪቱን መጪ ጊዜ ብሩህ ተስፋ አካል ነው” ሲል አስተያየቱን መስጠቱን አመልክቷል፡፡