ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ፣ ቀድሞ “የመለስ ዜናዊ የአመራር አካዳሚ” ይባል የነበረውን ተቋም ስያሜ “የአፍሪካ የአመራር ልህቀት ማዕከል” በሚል እንዲሰየም ውሳኔ አስተላልፏል።
ጠ/ሚ/ ዐቢይ አህመድ ዛሬ በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው እንዳስታወቁት፣ ምክር ቤቱ ስያሜውን የመቀየር ውሳኔ ላይ የደረሰው “የአካዳሚው የስም ለውጥ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የአመራር ጥያቄዎችን ማሟላት የሚያስችል ዐቅም ያላቸውን ልሂቃን የሚያፈራ እና የዕድገት ተኮር
አስተሳሰብን የሚያንፀባርቅ የትምህርት ተቋም እንዲሆን በማሰብ ነው።
ከዚህ በፊት ተቋሙን እንዲመሩ ተመርጠው የነበሩት የቀድሞው የአማራ ክልል ብልጽግና ጽ/ቤት ኃላፊ ዮሐንስ ቧያለው “ተቋሙን አሁን ባለው ስያሜ እና ብራንድ ለማገልገል ዝግጁ አይደለሁም” በማለት ሹመቱን እንደማይቀበሉ መግለጻቸውና በወቅቱ የብልጽግና ፓርቲ የህዝብና የውጭ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ የነበሩት አቶ አወሉ አብዲ የአካዳሚው ፕሬዝዳንት ሆነው በጠ/ሚ/ር ዐቢይ መሾማቸው የሚታወስ ነው፡፡