ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል አሊዲኒ አለሳ ዛሬ እንደተናገሩት፣ በክልሉ ፈንቲ-ረሱ ዞን እዋ ወረዳ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱን ለማወክ ሞክረዋል የተባሉ 3 ግለሰቦች በእሰራትና ገንዘብ እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል።
ግለሰቦቹ በእዋ ወረዳ አንድ ምርጫ ጣቢያ ህጋዊ እውቅናና ውክልና ሳይኖራቸው እራሳቸውን የምርጫ ታዛቢ አድርገው በመንቀሳቀስ ሁከት ለመፍጠር በመሞከራቸው፣ የድምጽ አሰጣጡን ሂደት ለማወክ በመሞከር ጥፋት በቁጥጥር ስር ውለው በአቃቤ ህግ በኩል በፍርድ ቤት ክስ እንደተመሰረተባቸው የተናገሩት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል አሊዲኒ አለሳ፣ በክሱ መሰረትም ጥፋተኝነታቸው በማስረጃ በመረጋገጡ፣ የእዋ ወረዳ ፍርድ ቤት ትናንት በዋለው አስቸኳይ ችሎት ሶስቱ ግለሰቦች እያንዳንዳቸው በአንድ ዓመት እስራትና አንድ ሺህ ብር እንዲቀጡ መወሰኑን አስታውቀዋል።
በተመሳሳይ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ወረዳ ሁለት ውስጥ የጓደኛውን ምርጫ ካርድ ቀምቶ በህዝብ ፊት በመቅደዱ የተከሰሰ ግለሰብ፣ በአንድ ሺህ ብር ገንዘብ መቀጣቱ የተገለጸ ሲሆን፣ በጎንደር ከተማ ወደ ምርጫ ጣቢያ የሄዱ ግለሰቦች ቤት ሰብሮ በመግባት ጥሬ ገንዘብ የዘረፈ መሃመድ ሃሰን የተባለ ሌላ ግለሰብም በ1 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጣ እንደተወሰነበት የከተማዋ አስተዳደር አቃቤ ህግ አስታውቋል።