ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው መግለጫ፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከመቀሌ መውጣቱን ተከትሎ ከተማዋ በክልሉ ሀይሎች ቁጥጥር ስር መሆኗን ጠቅሶ “በክልሉ የሚገኙ ሲቪል ዜጎች ደህንነት ያሳስበኛል” ብሏል።
“ባለፉት ወራት በክልሉ በነበረው ግጭት የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ጨምሮ በንፁሀን ላይ አስከፊ ጉዳት ተፈጽሟል። በአሁኑ ሰዓት የክልሉ ሀይሎች አካባቢውን መልሰው መቆጣጠራቸውን ተከትሎም በንፁሀን ላይ የበቀል ጥቃት እንዳይፈፀምና የጦር ወንጀሎች እንዳይፈፀሙ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል” ያለው የአምነስቲ መግለጫ፣ በክልሉ ሰብአዊ ዕርዳታዎች ባልተገደበ መልኩ ተደራሽ እንዲሆኑ ማረጋገጥ እንደሚገባና በአሁኑ ሰዓት ተቋርጦ የሚገኘው የኢንተርኔት አገልግሎት፣ የህትመት ወይም የብሮድካስት ሚዲያ ተደራሽነትን ወደነበረበት እንዲመለስ “ሁሉም አካላት እንዲተባበሩ” ሲልም ጥሪ አቅርቧል፡፡