እኔ ለምርጫ በተወዳደርኩበት አራዳ ክፍለ ከተማ ምርጫ ክልል 1/9 ውስጥ 5 ልጆች ያሏቸው አንዲት እናት አሉ። አንዳንድ ሰዎች “እማማ ምርጫ ቦርድ” እያሉ እንደሚጠሯቸው የሰማሁት በምርጫው ምሽት ነበር። ነገሩ እንዲህ ነው።
“እማማ ምርጫ ቦርድ” ካሏቸው አምስት ወንዶች ልጆች አንደኛው የወረዳችን የኢዜማ አባል እና የምርጫ አስተባባሪ ነው። ታናሽየው ደግሞ የብልጽግና አባል እና ምርጫ አስተባባሪ ነው። አንደኛው ወንድም የባልደራስ ሌላኛው የአብን አባላት ሲሆኑ የመጨረሻው ወንድማቸው የየትኛውም ፓርቲ አባል ያልሆነ የፓሊስ አባል በመሆኑ እናታቸውን የሠፈሩ ሰዎች “እማማ ምርጫ ቦርድ” ብለው ስም እንዳወጡላቸው ሰምቻለሁ። ሁሉንም አቅፈው ያኖራሉና!
በምርጫው እለት ምሽት ላይ በድምጽ መስጫው ድንኳን ጀርባ የብልጽግና አባል የሆነው ወንድም በሴፍቲኔት የተደራጁ እናቶችን አሰልፎ ማንን እንደሚመርጡ ነግሮ፤ የምርጫ ምልክቱን አስጠንቶ፤ አሰልፎ ሊያስገባቸው ሲል የኢዜማው አባል ወንድሙን እጅ ከፍንጅ ይይዘዋል። “ይህ ሕገወጥ ተግባር ነው” ሲል ከወንድሙ ጋር አንገት ለአንገት ይያያዛሉ። ገላጋይ ከሆኑት የጸጥታ አስከባሪዎች አንዱ ፓሊስ ሌላኛው ወንድማቸው ነበር። የኢዜማው ወንድም ከሰሰ። ፖሊሱ ወንድም ጸጥታ አስከባሪ ሆነ። የብልጽግናው ወንድም ታሠረ። የምርጫው እለትም አለፈ።
ምርጫው ብዙዎቻችን እንደታዘብነው “ነፃ እና ዴሞክራሲያዊ” የሚለው ማሞካሻ ለጊዜው ይቆየን እና ቢያንስ ሰላማዊ ሆኖ ተጠናቀቀ። ምርጫውን ተከትሎ ድንጋይ አለመወራወራችን፣ መንገድ አለመዘጋቱ፣ ጥይት አለመተኮሱ በራሱ ለሀገራችን እንደ በጎ ጅምር ሊወሰድ ይገባል። በበኩሌ ምርጫ የሚገነባ ባህል እና ሂደት እንጂ ውጤት አይደለምና ድሉ በሂደቱ በጎ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ተዋንያን ሁሉ ነው እላለሁ።
የምርጫው ውጥረት ስሜት ረገብ ሲል በሦስተኛው ቀን ታናሽየው ከእስር ተፈትቷል። የአራዳ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ካህናት እማማ ምርጫ ቦርድ” ቤት ሽምግልና ተቀመጡ። የተጣሉ ወንድማማቾችን ሰብስበው አስታረቁ። የተለያዩ ፓርቲዎች አባላት እና ደጋፊ የሆኑት ወንድማማቾች እርቀ ሰላም አውርደው ተስማምተው ዛሬ በሰላም ኑሮአቸውን በአንድ ጣርያ ሥር ቀጥለዋል። ምናልባትም 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ እስኪደርስ በፉክክር ሳይሆን በትብብር እንደየአቅማቸው እናታቸውን “እማማ ምርጫ ቦርድን” እየደገፉ ይቀጥላሉ። ኢትዮጵያን ሳስባት እማማ ምርጫ ቦርድን ትመስለኛለች።
ሌላ አንድ ገጠመኝ ልጨምርላችሁ። በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ ገዛኸኝ ደግፌ እና ታረቀኝ ደግፌ የተባሉ የአንድ እናት እና የአንድ አባት ልጆች፤ ወንድማማቾች አንደኛው ኢዜማን ሌላኛው ብልጽግናን ወክለው በዕጩነት ተወዳዳሪ ሆነው ነበር። የኢዜማ እጩ የሆነው ታናሽዬው ታረቀኝ ደግፌ ታላቅየውን ለማለፍ ችሏል።
የሀገራችን ሰው “ቤት ጣርያ የሚከድኑ ሣር አይሻሙም” ይላል። የቤቱ ጣርያ በአንዱ በኩል ተከድኖ በአንዱ በኩል ሳይከደን ቢቀር ቤቱ ያፈሳልና።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ኢትዮጵያ የምትባል የጋራ ጎጆ ለማቆም በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚደክሙ የአንድ ሀገር ልጆች፤ ሠራተኞች እንጂ ደመኞች አይደሉም። ዓላማቸው በሀቀኝነት ለሀገር አንድነት እና ለሕዝብ ሰላም እስከሆነ ድረስ የሚያስተባብራቸው እንጂ የሚያናክሳቸው አንዳች ምክንያት አይታየኝም።
ትናንት ምሽት የሀገሪቱ ምርጫ ቦርድ የምርጫውን ውጤት አሳውቋል። የምርጫው ውጤት የናፈቅነውን ዝንጉርጉር ፓርላማ ባያሳየንም የጀመርነው የዴሞክራሲ መሠረት ላይ እየገነባን ከመሄድ ውጪ የተሻለ አማራጭ ያለን አይመስለኝም።
የኢዜማ አባላት እና ደጋፊዎች እስከ ድምጽ መስጫው ቀን ድረስ በከፍተኛ የፉክክር መንፈስ እንደ ወዛደር መሬት ወርደን ሠርተናል። ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ከድምጽ መስጪያው ማግሥት ጀምሮ ግን ቃላችንን ጠብቀን ሀገርን ወደማረጋጋት እና የሕዝብ ሰላምን አስቀድመን በመሥራት ያሳየነው ጨዋነት የድምጽ ብልጫ ተወስዶብን ቢሆን እንኳን የሀሳብ ብልጫችንን ይዘን እንድንቀጥል አድርጎናል።
የልፋታችንን ያህል ባይሆንም በፓርላማ ውስጥ የምንወከልበት ጥቂት ወንበሮች አሸንፈን ይሆናል፤ የሕዝብ ልብ ውስጥ ብዙ ወንበሮችን አሸንፈናል ድሉ የእኛም ነው። በዚያ ላይ ደግሞ ጷግሜን ላይ በቀሪ ምርጫ ጣብያዎች ላይ እንፎካከራለን። ከዓመት በኋላም የቀበሌ እና የአካባቢ ምርጫ ይጠብቀናል። ወገባችንን አሥረን ወደሥራ ገብተናል።
እማማ ኢትዮጵያ የምትባል የጋራ ጎጆአችንን ማቆም የሁላችንም የቤትሥራ ነውና ሀገር እና ሕዝበን በማስቀደም ትግሉ ሰላማዊ ሆኖ ይቀጥላል።
#ሕይወት_ይቀጥላል
#ኢትዮጵያ_ታሸንፋለች