የታላቅ ሀገር ዜጋ ስትሆን እንዲህ ነው፡፡ ሴትየዋ አልደበቁም፡፡ ‹‹ወደ ኢትዮጵያ የምሄደው ሁለት አላማ ይዤ ነው፤ የመጀመሪያው፣ ወደ ትግራይ ክልል ለመግባት የሚያስችሉ መንገዶች ሁሉ ተከፍተው የሰብአዊ እርዳታ በሰፊው እንዲደርስ ለማድረግ ሲሆን፣ ሁለተኛው የኢትዮጵያ መንግስት ከህወሀት ጋር ድርድር እንዲያደርግ ለማግባባት ነው፡፡›› ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት እነዚህን ሁለት ነጥቦች ቢቀበል ኢትዮጵያ የእነኢራቅ፣ ሶማልያ፣ ሊቢያና የመንን ቡድን ትቀላቀላለች፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ግልጽ ነው፡፡ የምእራባውያን ትልቁ ግብ የሱዳንን ድንበር ከኢትዮጵያ አስለቅቆ ለትህነግ የመሳሪያና የሰው ሀይል ማስገባት ነው፡፡ ድንበሩ ተከፈተ ማለት ሱዳን፣ ግብጽና ምእራባውያን ያለ ምንም ችግር ትግራይ ገቡ ማለት ነው፡፡ በአፋር በኩል ትግራይ ክልል ድንበር የደረሰ እርዳታ እንዳይገባ እያስተጓጎለ ያለውን ትህነግ እሽሩሩ እያሉ፣ ‹‹እርዳታ እንዲገባ የሱዳንን ድንበር ክፈቱ ማለት›› ትንተና የማይጠይቅ ሸፍጥ ነው፡፡
በጣም የሚገርመው ደግሞ ሁለተኛው ነጥብ ነው፡፡ የሎከርቢውን የአይሮፕላን ፍንዳታ ያቀነባበረችውን ሊቢያን በማእቀብ አድቅቃ በመጨረሻም በማፍረስ፣ የ9/11 ጥቃትን ያቀናበረውን ቢንላደንን የገባበት ገብታ በመግደል፣ አይነኬ ሉአላዊ ሀገር ነኝ የምትለው አሜሪካ፣ የኢትዮጵያን መንግስት በመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ከፈጸመው ትህነግ ጋር እንዲደራደር ለመጠየቅ አለማፈሯ የሚያሳየው አሜሪካ ጥቅሟን ለማስከበር የማትድጠው ሰብአዊ እሴት እንደሌለ ነው፡፡ አሜሪካ አሁን ያለው የኢትዮጵያ መንግስት (እንደቀደመው መንግስት) በምስራቅ አፍሪካ የጥቅሟ ቃፊር እንደማይሆን አውቃለች፤ ስለዚህ ይህን መንግስት በፍላጎቷ ስር ለማንበርከክ ወይም ለማስወገድ ኢትዮጵያን እስከማፍረስ ትሄዳለች፡፡ . . . . .. . ለዛሬዋ ኢትዮጵያ አሜሪካ፣ ግብጽና ምእራባውያን ሲኦል ናቸው፤ ትህነግ፣ ‹‹ኢትዮጵያን ለማፍረስ እስከሲኦል እንሄዳለን›› ሲል እነዚህን ሀገራት ማለቱ ነው፡፡
ነገሮች እየከፉ ከሄዱ ኢትዮጵያ ያላት ምርጫ ሁለት ይመስለኛል፡፡ አንድ፣ ድንበሯን ከፍታ በምእራባውያንና በትህነግ በሚፈጸምባት ጥቃት መተራመስ (ከተሳካላቸው መፍረስ)፤ ሁለት የአሜሪካንና የምእራባውያንን ማእቀብ መቀበልና ከሚፈጥረው የድህነት ጫና ጋር መጋፈጥ፡፡ ኩባና ኤርትራ ይህን ጫና ተቋቁመው ሉአላዊነታቸውን አስከብረው ሀገር ሆነው ቀጥለዋል፡፡ እንደሊቢያና የመን ያሉት ደግሞ በምእራባውያን ሴራ ተከፋፍለው እንደ ሀገር ፈርሰዋል፡፡
አዎ፤ ማእቀብ ድህነታችንን ያብሰዋል፤ እንራባለን፤ ታመን ለመዳን መድሀኒት እንቸገራለን፡፡ ይህን ፈርተን ግን ለልጆቻችን የምንተዋት ኢትዮጵያ ዳቦና መድሀኒት ያላት የተዋረደችና የተናቀች ልትሆን አይገባም፡፡ እኛ ከአባቶቻችን የተረከብናት ሀገር፣ በአለም አደባባይ አንገቷን ቀና አድርጋ የምትቆም፣ የተከበርችና የታፈረች፣ ድሀ ሀገር ናት፡፡ ከቻልን ካለችበት ድህነት ለመነሳት ትንጠራራ ዘንድ ቢያንስ የጀመርነውን ግድብ ጨርሰን፣ ካልሆነም እንደተረከብነው ሉአላዊነቷን ጠብቀን፣ ሀገራችንን ለልጆቻችን ማቆየት አለብን፡፡ ይህ ደግሞ አንድነትንና አፈር ግጦ መነሳትን ይጠይቃል፡፡