ለሰብዓዊ መብቶች መከበርና ለሀገር መረጋጋት የቀረበ ጥሪ

ለሰብዓዊ መብቶች መከበርና ለሀገር መረጋጋት የቀረበ ጥሪ

አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ

ነሀሴ 04 ቀን 2013 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) በትግራይ ክልልና አዋሳኝ አካባቢዎች እየተስፋፋ ያለውን ጦርነት ጨምሮ በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች ያለው የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ እጅግ እንደሚያሳስበው ከዚህ ቀደም ባወጣቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎች ሲገልፅ ቆይቷል፡፡ የጦርነቱ መስፋፋት ኢሰመጉ መንግስት ከሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በትግራይ ከልል የተናጠል ተኩስ አቁም ማድረጉ ለሰላም ሲባል የተደረገ ጥረት መሆኑን በመገንዘብ እርምጃውን ያደንቃል። በሌላ በኩል በትግራይ ክልል እየተንቀሳቀሰ ያለው ኃይል ጦሩን ወደ አማራ እና አፋር ክልል በማስጠጋትና ተኩስ በመክፈት ለበርካታ ዜጎች ሕይወት መጥፋት፣ የአካል መጉደል፣ መፈናቀል እና የንብረት ዝርፊያ እንዲሁም ውድመት ምክንያት ሆኗል።
በተፈናቃዮች ላይ የተፈፀመ ጥቃት በጦርነቱ ሳቢያ እስከ አሁን ባለው መረጃ መሰረት የተፈናቃዮች ቁጥር ከ300 ሺ በላይ መድረሱን እና ደህንነታቸውም አደጋ ላይ መውደቁ ኢሰመጉን አሳስቦታል፡፡ በተለይም ከሰሞኑ በአፋር ክልል በጋሊኮም ጤና ጣቢያና ት/ቤት ተጠልለው በሚገኙ ተፈናቃዮች ላይ በደረሰው ጥቃት ሕጻናትን ጨምሮ ከ200 በላይ ንጹሃን
ዜጎችን ህይወት የቀጠፈ ድርጊት ያደረሰው ሰብዓዊ ጥፋት እንዲሁም ለተፈናቃዮች ይሆን ዘንድ በመጠለያ ጣቢያ
የነበረውን የምግብ እና መሰል የሰብዓዊ ድጋፍ ቁሳቁስ እርዳታውን ለሚሹ ሰዎች ድጋፍ ሳይውል መውደሙ ኢሰመጉን አሳዝኗል።
ህጻናትን በጦርነት ማሳተፍ በትግራይ ክልል እየተንቀሳቀሰ ያለው ኃይል አገራዊ፣ አህጉራዊ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ህግጋትን በተፃረረ መልኩ ሕፃናትን የጦር መሳሪያ በማስያዝ በግጭት ውስጥ ማሳተፉ ተገቢ አለመሆኑን ገልፆ ድርጊቱ እንዲገታ ኢሰመጉ ከዚህ ቀደም ባወጣው መግለጫ ላይ ማሳሰቡ ይታወሳል፤ በዚህ አይነት እንቅስቀሴ ውስጥ እንዲሳተፉ የተደረጉ ሕፃናትም ሕይወታቸው ያለፈ እና የአካል ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች ለመረዳት ተችሏል። ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ በሕፃናት ላይ ሊደርስ የሚችለው ጉዳት ኢሰመጉን በእጅጉ ያሳስበዋል።

የኢሰመጉ ጥሪ
ስለዚህም ሀገራችን የገባችበት አጣብቂኝ እና ፈታኝ ሁኔታ አፋጣኝ ምላሽ የሚሻ ስለሆነና እየደረሰ ያለው ሰብዓዊ ጥፋትም ባፋጣኝ መቆም ስላለበት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሀገር የምትረጋጋበትንና ሰላም የሚሰፍንበትን መንገድ ለማግኘት መስራት እንዳለባቸው ኢሰመጉ ያምናል።
በመሆኑም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ያሉ ሁሉም አካላት ግጭቱን እና ሰብዓዊ ቀውሱን ከሚያባብሱ ተግባራት እንዲቆጠቡ እንዲሁም ለሀገር ሕልውናና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ቅድሚያ እንዲሰጡ ኢሰመጉ ጥሪውን ያቀርባል።
በመጨረሻም የሚመለከታቸው መንግሰታዊ ተቋማት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የማሕበረሰብ
አንቂዎች፣ ምሁራን፣ የመገናኛ ብዙሃን፣ የሲቪክ ማህበረሰብ አካላት፣ የፖሊቲካ ፓርቲዎች፣ በአጠቃላይ የሀገራችን ህዝብ በሀገራችን ውስጥ እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮች የሚፈቱበት ሁኔታ እንዲፈጠር እና በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች ሰላም እንዲሰፍን፣ የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ የበኩላቸውን ገንቢ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ኢሰመጉ ጥሪ ያቀርባል፡፡

ነሀሴ 04 ቀን 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

LEAVE A REPLY