የሱዳኑ ጠ/ሚር አብደላ ሀምዶክ የጠሯቸውን አምባሳደር || መሳይ መኮነን

የሱዳኑ ጠ/ሚር አብደላ ሀምዶክ የጠሯቸውን አምባሳደር || መሳይ መኮነን

የሱዳኑ ጠ/ሚር አብደላ ሀምዶክ የጠሯቸውን አምባሳደር ወደአዲስ አበባ እንዲመለሱ ካደረጉ በኋላ በጽ/ቤታቸው አማካኝነት መግለጫ ሰጥተዋል። በዚህም ኢትዮጵያ ሰላም እንድትሆን እንደሚመኙ፣ በእነሱ የችግር ጊዜ ጠ/ሚር አብይ የዋሉት ውለታን በመጥቀስ ላደራድራችሁ ሲሉ በድጋሚ ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ምላሽ እንደ ቀድሞ አሁንም ‘እምነት ያጎደለ ለሽምግልና አይበቃም’ የሚል እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ። የሱዳን እንዲህ የሙጥኝ ማለት ግራ የሚያጋባ ነው። በድንበሩና በግድቡ በሁለት ግንባሮች ጉድጓድ እየማሰችልን በጎን ላደራድራችሁ ዓይነት ንዝነዛ የጤና አይመስለኝም።

ሰላምን የሚጠላ ክፉና ሴጣናዊ መንፈስ የተጠናወተው የህወሀት ዓይነት ቡድን ካልሆነ በቀር ማሰብ ማገናዘብ የሚችል ሰው አያደርገውም። ድርድር እንደወረደ ሀሳቡን ከወሰድነው ምቾት የሚነሳ ነገርም አይደለም። ሰላምን የምር ለማምጣት ለሚደረግ ድርድር ጀርባ መስጠት ተገቢነት ላይኖረው ይችላል። የሰላም ብቸኛ መንገዱ ድርድር ነው የሚል አቋም ግን በራሱ ችግር ያለበት ነው። ስንቱ ድርድር ሀገራትን ያፈረሱ፣ ጉልበተኞችን ያነገሱ፣ ክፉዎችን አሸናፊ ያደረጉ እንደሆነ በዓይናችን አይተን፣ ታሪክንም ገልበጥ አድርገን የምንመሰክረው እውነት ነው።

ሰላምን በጦርነት ያመጡ፣ በሴራ የተወጠረን ድርድርና ሽምግልና ወደጎን ገፍተው በመስዋዕትነት ሰላማቸውን ያረጋገጡ ሀገራትንም እንዲሁ አይተን፣ ታሪክ አንብበንም ታዝበናል። ጦርነት ለሰላም በግርድፍ ሲመለከቱት የሚጎረብጥ ይመስላል። ግን ከድርድር ይልቅ ፍትሃዊ ጦርነት ዘላቂ ሰላም ያመጣላቸውን ሀገራት እውነታ ስናጤን እሾህን በእሾህ ትክክለኛ መፍትሄ የሚሆንበትን አጋጣሚ መዘንጋት አይገባንም።

የሱዳን ዳግም ጥሪ ጥርጣሬን ይበልጥ የሚጭር ነው። ለምን በተደጋጋሚ ጥያቄውን አቀረበች? እውነት ለሰላማችን ተጨንቃ? በጦርነቱ ምክንያት በስደተኞች እጥለቀለቃለሁ ብላ ሰግታ? ኢትዮጵያ ምድር ላይ የሚጮኸው ጥይት እኔንም ይመታኛል ብላ ፈርታ? ሱዳን በአንድ ፊቷ የእናንተን ሰላም ስለምሻ ላደራድራችሁ የሚል ጥያቄ አከታትላ ትልካለች። በሌላ ፊቷ ደግሞ ከህወሀትና ከግብጽ ጋር ተቀናጅታ ለኢትዮጵያ ቀብር ጉድጓድ ትቆፍራለች። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በውጭ የሚገኙ የህወሀት መሪዎች ካርቱም የሚመላለሱት ለመዝናናት አይደለም።

ሀምዳይት በተሰኘ አከባቢ በሺዎች የሚቆጠሩ የህወሀት ታጣቂዎች እየሰለጠኑ ያሉት የዳርፉሩን ሰላም ለማስከበር ነው እንደማይሉን ተስፋ እናደርጋለን። ከአባይ ግድብ ትይዩ በሱዳን ድንበር ገባ ብሎ በሚገኝ ቦታ ላይ “የስደተኞች መቀበያ” በሚል የተከፈተው ካምፕ ዋና ዓላማው ምን እንደሆነ ያላወቅን የመሰለው ካለ ቂል ነው። ከግብጽ ጋር እፍ ያለ ፍቅር ውስጥ የገባችው ሱዳን ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት ነው እንዲህ የምለፋው እንደማትለን እርግጠኛ ነኝ። ጥቅምት 24 ህወሓት ሰሜን እዝን ባጠቃ በሶስተኛው ቀን ጦሯን ወደኢትዮጵያ ድንበር አስገብታ ወረራ መፈጸሟን እንደ ውለታ እንድንቆጥርላት እያሰበች ከሆነም ሱዳን ጨርቋን ጥላ አብዳለች እንጂ ሌላ የሚያሰኝ አይደለም። ሌላም… ሌላም።

ሁለት ነገሮች ይነሳሉ። በቅድሚያ ድርድር ያስፈልጋል ወይ? አሁን ኢትዮጵያ የገባችበት ጦርነት በድርድር ወደ ሰላም የሚቀየር ነው? የሚለው አንደኛው ነው። በግሌ ቢሆን እመርጣለሁ። ሆኖም ድርድር ሁሌም ሰላምን አያስገኝምና ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ በድርድር ይፈታል የሚል እምነት ፈጽሞ የለኝም። ለዚህ ሺህ ምክንያቶችን ማስቀመጥ ይቻላል። ህወሓት የሚባልን ክፉና የአረመኔዎች፣ ማፊያዎች ስብስብ የሆነን ቡድን በቅጡ ለሚያውቅ ድርድር እንደውም ሰላምን አርቆ ለመቅበር የሚረዳ መሳሪያ ይሆንበታል። ከህወሀት ጋር ቁጭ ብሎ መደራደር ኢትዮጵያን ለእርድ አሳልፎ እንደ መስጠት የሚቆጠር ነው። የህወሀት ጉዳይ የሚፈታው በሚገባው ቋንቋ በማናገር ብቻ ነው። ህወሓት መሸነፍ አለበት። ህወሓት መወገድ አለበት። በየትኛውም ፎርም የሚመጣ ህወሓት ለኢትዮጵያን ካንሰር ነው። ህወሀትን አስቀምጦ ስለኢትዮጵያ ሰላምና እድገት ማሰብ ፈጽሞ የሚሆን አይደለም። አራት ነጥብ።

ሁለተኛው ጉዳይ አንደኛው ላይ የሚጠናቀቅ በመሆኑ መዘርዘር ጥቅም አይኖረውም። ድርድር አያስፈልግም ከተባለ አለቀ፣ ደቀቀ ማለት ነው። ቢያስፈልግ እንኳን አሜሪካን በቀመረችው፣ ሱዳን እንድታስፈጽመው ከዋሽንግተን ዲሲ በተቀበለችው መመሪያ የሚደረግ ድርድር ለኢትዮጵያ የተሳለ ካራ እንጂ የሰላም መንገድ አይደለም። ሁለቱም ሀገራት በኢትዮጵያ ጉዳይ ተፈትነው ወድቀዋል። አሜሪካንም ሆነች ሱዳን ህወሀትን ከመቃብር እንዲወጣና ነፍስ ዘርቶ የኢትዮጵያ ክፉ ደዌ ሆኖ እንዲቀጥል የአንበሳውን ድርሻ ወስደዋል። አሁንም ህውሀትን ቤተመንግስት ካላስገባንና ዳግም ካላነገስነው ሞተን እንገኛለን ሩጫ ውስጥ እየዳከሩ ናቸው። አሜሪካ በዲፕሎማሲውና በጫናው፣ ሱዳን ደግሞ ለህወሀት ሽብር ፈጻሚዎች ማሰልጠኛ ቦታ በመስጠትና በማስታጠቅ የኢትዮጵያ ቀውስን ቤንዚን እያረከፈከፉበት እንደሆነ የአደባባይ ሀቅ ነው። እና ከእባብ እንቁላል እንዴት ብለን እርግብ እንጠብቅ?

ኢትዮጵያ በያዘችው መንገድ ትቀጥላለች። ህወሀት ከትግራይ ህዝብ ጫንቃ እስኪወገድ እርምጃው ለአፍታም ሳይዘናጋ የሚካሄድ እንደሚሆን አምናለሁ። በዚያ መንገድ ብቻ ነው የህወሀትን እብደት ማስታገስ የሚቻለው። በተጀመረው አካሄድ ብቻ ነው ህወሀት ኢትዮጵያ ላይ የደቀነውን ብርቱ ስጋት ማስወገድ የሚቻለው። ህወሓት ሌላ ምርጫ እንዳይኖረን አድርጎናልና።

LEAVE A REPLY