ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– አራት ኪሎ በሚገኘው ጠቅላይ ቤተ ክህነት ግቢ በንብረት ግምጃ ቤት ውስጥ የተቀመጠ ከ1 ሺህ 800 በላይ ጥይት በህዝብ ጥቆማ እና ፖሊስ ባደረገው ብርበራ ተይዟል፡፡
የህወሓት ቡድን ለሽብር ተግባሩ የሚጠቀምባቸውን የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች በተለያዩ የኃይማኖት ተቋማት ውስጥ እያከማቸ እና በኃይማኖት ሽፋን የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ግለሰቦችን በተላላኪነት እያሰማራ በበርካታ ንፁሃን ላይ አሰቃቂ እልቂት ሲፈፅም እንደቆየ ይታወቃል፡፡
ይህን የሽብር ቡድኑን ሴራ የተረዳው የከተማዋ ነዋሪ በተለያዩ ቦታዎች የሚመለከታቸውን አጠራጣሪ ጉዳዮችን ለፀጥታ አካላት ጥቆማ እየሰጠ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡
ህዳር 8 ቀን 2014 ዓ.ም በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 በሚገኘው ጠቅላይ ቤተ ክህነት ግቢ ውስጥ በህዝብ ጥቆማ እና ፖሊስ ባደረገው ብርበራ ከ1ሺህ 800 በላይ ጥይት ተይዟል፡፡
በቤተ ክህነቱ ግቢ በሚገኝ የንብረት ግምጃ ቤት ባለ የፅህፈት እና የፅዳት እቃዎች ማስቀመጫ ውስጥ በተደረገው ብርበራ የተገኘው 1 ሺህ 363 የብሬን እና 493 የሽጉጥ ጥይት ነው የተያዘው።