ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በአዲስ አበባ በአንድ ግለሰብ የሸቀጣ ሸቀጥ መደብር ውስጥ ተቀጣጣይ ቁሳቁስና ኬሚካሎች መያዛቸው ተገለፀ፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊሰ ኮሚሽን ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በአሁኑ ወቅት ነዋሪነቱን በሳውዲ አረቢያ ያደረገ አቶ መሀመድ ሀሰን የተባለ ግለሰብ ተቀጣጣይ ቁሳቁስና ኬሚካሎችን ሸቀጣ ሸቀጦችን እንደሽፋን ተጠቅሞ በመደብሩ ውስጥ ደብቆ የተገኘ መሆኑን ጠቅሷል፡፡
ግለሰቡ ከሀገራዊ ለውጡ በፊት ለሽብርተኛው ሕወሓት በርካታ ገንዘብ በመላክ ከጁንታው አመራሮች ጋር የጥቅም ትስስር በመፍጠር “ተቀጣጣይ ማቴሪያሎችና ኬሚካሎች ችርቻሮ ንግድ” በሚል ፍቃድ አውጥቶ ሲንቀሳቀስ እንደነበር ያስታወቀው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ግለሰቡ ይሄንን የንግድ ፈቃዱን ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ ደግሞ “የሸቀጣ ሸቀጥ ችርቻሮ ንግድ” በሚል ቀይሮ ሲንቀሳቀስ የቆየ መሆኑን አመልክቷል፡፡
የደህንነትና ፀጥታ አካላት ጉዳዩን በጋራ ሲከታተሉ ከቆዩ በኋላ የግለሰቡ የሸቀጣ ሸቀጥ ችርቻሮ ንግድ መደብር በሚገኝበት በአዲስ አበባ ከተማ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ቀጠና 5 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተደረገ ፍተሻ በርካታ ተቀጣጣይ ቁሳቁስና ኬሚካሎች መገኘታቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም መደብሩ እንዲታሸግ ተደርጎ በፖሊስ አባላት እንዲጠበቅ መደረጉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በመግለጫው ጠቁሟል፡፡