ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በውስጥና በውጭ ሃይሎች የጋራ ጥምረት የተጋረጠባትን አደጋ አስወግዳ ሰላምና ደኅንነቷን ታረጋግጣለች ሲሉ ዴንማርካዊው ፕሮፌሰር ቶቢያስ ሃግማን ተናገሩ።
ኢትዮጵያን የተመለከቱ በርካታ መጽሃፍትን የጻፉት ፕሮፌሰር ቶቢያስ ሃግማን በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከኢዜአ ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያ አሁን የተጋረጠባትን አደጋ አልፋ ሰላምና ደኅንቷን ማረጋገጥ ትችላለች የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ከፍተኛ ሕዝባዊ ቅቡልነት ያለው በመሆኑ በአሸባሪው ህወሓት የተደቀነውን አደጋ መቀልበስ እንደሚችል ተናግረዋል።
አሁን ኢትዮጵያ የገጠማት ችግር ሊቢያ፣ የመንና ሶሪያ ካጋጠማቸው ችግሮች ይለያል ያሉት ፕሮፌሰሩ የኢትዮጵያ ችግር የሚቀለበስ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥትም ከእነዚህ አገራት በተቀራኒው ሕጋዊና ሕዝባዊ ቅቡልነት ያለው እንዲሁም አቅም ያለው መንግሥት መሆኑን ነው ያስረዱት። ኢትዮጵያ እንደሌሎቹ አገራት ቅኝ ያልተገዛች አገር መሆኗም ለየት እንደሚያደርጋትና ይህም ኢትዮጵያ በቀላሉ ወደ ቀድሞ ሰላሟ እንደምትመለስ ያስችላታል ብለዋል።
የኢትዮጵያን መንግሥት መደገፍ የሚገባቸው የውጭ ሃይሎች በተቃራኒው አሸባሪውን ህወሓት መደገፋቸውን ገልጸው ይህም ሊስተካከል እንደሚገባ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰላም ማምጣት ከተፈለገ የኢትዮጵያን መንግሥት መደገፍና ማገዝ ይገባል ነው ያሉት።
አሸባሪው ሕወሓት ሥልጣን ላይ በነበረበት 27 ዓመታት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እየፈጸመ መቆየቱንም አስታውሰዋል።