ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የህወሃት የሽብር ቡድን በአዲስ አበባ እና በዙሪያው ለሽብር ተግባር ያሰማራቸው ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ።
በከተሞች በህብረተሰቡ ውስጥ በተለያዩ መንገዶች በመመሳሰል እንዲገቡ በማድረግ አዲስ አበባ እና በዙሪያው ተልእኮ ሰጥቶ በማስገባት ለሽብር ተግባር እየተንቀሳቀሱ መሆኑን እንደተደረሰበት የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር መላኩ ፈንታ ገልጸዋል።
የሽብር ቡድን አባላቱን በንግድ ተቋማት፣ በመንግስት መስሪያ ቤቶች እና በሌሎችም የሙያ ስራዎች ህብረተሰቡ ውስጥ ተሰግስገው እንዲገቡ በማድረግ አዲስ አበባን እና አካባቢውን ለማተራመስ አቅዶ እየሰሩ መሆኑ ተደርሶበት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በዚህም ቡድኑ ለሽብር ተልእኮ ያሰማራቸው በርካታ ግለሰቦች በርካታ ተተኳሽ ጥይቶች ከነፍስ ወከፍ እና የቡድን የጦር መሳሪያ ማለትም ቦንቦች ተቀጣጣይ ፈንጂዎች እንዲሁም የሀገር ውስጥና የውጭ ገንዘቦችን ይዘው በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም አብራርተዋል።
የተለያዩ የክልል እና የፌዴራል የፀጥታ መዋቅራት አልባሳትን ከነአርማው በማልበስና የተለያዩ የጦር ሜዳ ንድፍ መነፅር እና ሌሎችንም ቁሳቁሶችን በመጠቀም አሳሳስቶ ለመልበስ መሞከሩን ፖሊስ ባደረገው ፍተሻ ማገኘቱን ገልጸዋል።