ኢትዮጵያ ነገ ዜና || አሜሪካና አጋሮቿ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በእነሱ ይሁንታና ቁጥጥር ስር ማዋል ባለመቻላቸው አገሪቱንም ሆነ ቀጣናውን ማተራመስ መምረጣቸውን የአፍሪካ የፖሊሲ ጉዳዮች ተንታኝ ላውረንስ ፍሪማን ተናገሩ።
አሜሪካ ዜጎቿን ከኢትዮጵያ ውጡ እያለች በምትወተውትበት ወቅት ወደ ኢትዮጵያ የመጡት አሜሪካዊው ፍሪማን ለኢፕድ እንደገለጹት አሜሪካና ተለጣፊ ምዕራባዊያን የመገናኛ ብዙኃን ኢትዮጵያ ላይ በውሸት የተመሰረተ የስነልቦና ጦርነት ከፍተዋል ብለዋል፡፡ ይህንን የሚያደርጉትም አቅደው እና መረጃን ሆን ብለው እያዛቡ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በባይደን አስተዳደር ውስጥ ለረጅም ጊዜ ከሕወሓት ጋር ግንኙነት የነበራቸውና አገሪቱን በእነሱ ቁጥጥር ስር አድርገው የነበሩ ሰዎች መኖራቸውን የገለጹት ፍሪማን ይህንን የበላይነታቸውን ስላጡና ወደነበረበት ለመመለስ ስለሚፈልጉ ነው ጫናውን እያደረጉ ያሉት ብለዋል።
የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ያለውን እውነታ ማመንም ሆነ እውነታውን መጋፈጥ አይፈልግም ሲሉም አክለዋል፡፡
በሕዝብ የተመረጠን መንግሥት ብሔር ተኮር በሆነና ባልተመረጠ አካል የመተካት ሂደትና አስተሳሰብ ከቀጠለ ለመላው አፍሪካ አደገኛ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የአፍሪካ ፖሊሲ ተመራማሪው ሎውረንስ ሌሊቱን ወደ አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ ባስተላለፉት የቲውተር መልዕክት ከተማዋ በአንዳንድ ምዕራባዊያንና የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ከተከፈተባት የስነልቡና ጦርነት ውጭ የተረጋጋችና መደበኛ እንቅስቃሴዋ ላይ ነች ማለታቸውን ዋልታ መዘገቡ ይታወሳል።