የተደቆሰው ህወሀት እያለ ጥቃት ደረሰብኝ ብላ ደረቷን እየደቃች የምታለቅሰው ሱዳን መሆኗን ለሚሰማ ግራ ይጋባል። የህወሀቱ ፍሰሃ ማንጁስ የለፋበት፣ እነስዬ አብረሃ ከአሜሪካን ካርቱም- ሀምዳይት እየተመላለሱ ፖለቲካቸውን(ዘረኝነታቸውን ቢባል ትክክለኛ መገለጫ ነው) የጋቱት፣ ሱዳን መሬት በማቅረብ፣ ግብጽ መሳሪያ በማስታጠቅ ያሰማሩት የትላንት የማይካድራው ጨፍጫፊ፣ የአሁኑ የህወሀት ተዋጊ ሰሞኑን በመተማ በኩል ሰተት ብሎ ሲገባ ለወሬ ነጋሪ እንዳይተረፍ ሆኖ ተደመሰሰ። ይህኔ ነው እንግዲህ ከካርቱም እሪታና ኋይታ የተሰማው። ካይሮም እንደካርቱም እዬዬውን አታቅልጠው እንጂ የውሽማ ለቅሶ ሆኖ በውስጧ አፍና ስቅስቅ ማለቷ የማይቀር ነው።
የመተማው ኦፕሬሽን በህወሀት መንደር ትልቅ ተስፋ የተጣለበት እንደነበረ ይነገራል። ለበርካታ ወራት ዝግጅት ተደርጓል። በሀምዳይት የስደተኞች ካምፕ የተሰባሰቡትን የማይካድራ ጨፍጫፊዎችን ጨምሮ ከተለያዩ ቦታዎች የተቀላቀሉት የትግራይ ተወላጆች ጠንከር ያለ ወታደራዊ ስልጠና ተሰጥቶአቸው በሱዳን ድንበር በኩል ኢትዮጵያን ለመውጋት ተዘጋጅተው ሲጠብቁ ነበር። ከአውሮፓ፣ አሜሪካና አውስትራሊያ የትግርኛ ድምጻውያን ሱዳን ድረስ ተጉዘው ትልቅ የማነቃቂያ መድረክ ለሰራዊቱ አቅርበው እንደነበርም ይታወሳል። በየፈረንጁ ከተሞች አውራጎዳናዎች ላይ ሲንከባለልና ሲንደባለል የሚውለው የህወሀት ደጋፊም ወርቅ ሀብሉን፣ ዶላር ዩሮውን ሳይሰስት እየሰጠ በገንዘብና በሞራል ከጎኑ የቆመለት ሃይል ነው።
እነስዬ አብረሃም ዘረኝነታቸውን አስታጥቀው የላኩትን ሃይል ቦስተን አሜሪካን ሶፋቸው ላይ ቁጭ ብለው በሪሞት ኮንትሮል ቴሌቪዥናቸውን እየቀያየሩ የመተማውን ድል ለመስማት ጓጉተው እንደነበር የሚታሙበት ጉዳይ ነው። ሱዳን፣ ግብጽና አሜሪካን ለዚህ ሰራዊት የተለያዩ ድጋፎችን ማድረጋቸውን ማስተባበል የማይችሉት የአደባባይ እውነት ሆኖ ታሪክ መዝግቦታል። እስከ30 ሺህ ይደርሳል የተባለው በሱዳን የሚገኘው የህወሀት ታጣቂ የኢትዮጵያን ሰራዊት በጀርባ በመውጋት ሰብሮ ገብቶ ውስጥ ካለው ሃይል ጋር ለመገናኘትና የሱዳኑን ኮሪደር ለማስከፈት ነበር ተስፋ የተደረገበት። ዋሽንግተን ዲሲ- ካይሮ- ካርቱም- መቀሌ በአንድ ገጽ ላይ ናቸው።
ይህ ሀይል የተወሰኑ አሃዶችን እየላከ በተደጋጋሚ የኢትዮጵያን በር አንኳኩቷል። በምዕራብ ጎንደር፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ፣ ለበርካታ ጊዜያት ጥቃት ከፍቶ ዱላውን ቀምሶ፣ ታጣቂዎቹን ለሙትና ለምርኮ ዳርጓል። የባለፈው ዓርብ በመተማ በኩል ያደረገው ሙከራ ግን በሰው ሃይልም ሆነ በመሳሪያ አቅም ተደራጅቶና ተዘጋጅቶ የመጣ ነበር። የኢትዮጵያ ሃይሎች አከርካሪውን ሰብረው፣ አብዛኛውን ታጣቂ ገድለው፣ ብዙውን ማርከው፣ ከቡድን አንስቶ ያሉ በርካታ መሳሪያዎችን በቁጥጥር ስር አድርገው ጥቂቱን ደግሞ እግሬ አውጪኝ አስፈርጥጠው ወደ ሱዳን መልሰው ሸኙት።
ይህ እንደተሰማ የህወሀት መንደር ማቅ ለበሰ። ባህር ማዶ ያለው ደጋፊም በያለበት በድንጋጤ ደርቆ ቀረ። በጀነራል አልቡርሃን ሰፈር ዜናው ጆሮን ጭው ያደረገ ሆኖ ደረሰ። የአልሲሲ ቤተመንግስትንም የሀዘን ድባብ ውጦት ነበረ። ክብርና ሞገስ ለኢትዮጵያ ሰራዊት ይሁንና የጠላቶቻችን ትልቁ ተስፋ እንደእንቧይ ካብ ተደረመሰና አረፈው። የሃምዳይቱ የህወሀት ሰራዊት አልቆለታል ባይባልም በቀላሉ እንዳያንሰራራ ተደርጎ ተደቁሷል ማለት ይቻላል። ከእንግዲህ ከሞከረ ግን ፍጻሜው መሆኑ አይቀርም። በእውነቱ ወገብ የሚቀነጥስ ኪሳራ ነው የገጠማቸው።
የሱዳን “ኢትዮጵያ አጠቃችኝ” ለቅሶ የመጣው በሶስት ምክንያቶች በአንዱ ወይም በሶስቱም ነው። አንደኛው እንደለመደችው የውስጧን ቀውስ ውጪያዊ በማድረግ የዜጎቿን ትኩረት ለማስቀየስ ነው። ሁለተኛው የድንበሩ ጭቅጭቅ ላይ ኢትዮጵያን ጠብ ጫሪ አድርጋ ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ለማሳየት የሚያስችላትን ነጥብ ለማስቆጠር ነው። ሶስተኛው ደግሞ ከመተማው የዓርብ እለት ጥቃት ጀርባ የለሁበትም፣ ከደሙ ንጹህ ነኝ የሚል መልዕክት ለመስደድ ነው። ሶስቱም ምክንያቶቿ ውሃ ባያነሱም ምርጫ የላትምና ማለት ያለባትን ብላለች። ለእኛ ግን መልዕክቱ ሲደርሰን ለህወሀት ሞት የተሰማ ለቅሶ ሆኖ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ሰሞኑን እንዳስታወቀውም ከሱዳን ጋር ምንም ዓይነት ጸብ ውስጥ አልተገባም። ለሱዳን ወታደር ተብሎ የተተኮሰ ጥይት የለም። የቀረበው ክስ መሰረተ ቢስ ነው። እንግዲህ የሱዳን እዬዬ ከህወሀት የመተማ ኪሳራ ጋር የተያያዘ መሆኑን አስረግጦ መግለጽ ይቻላል።
በተረፈ ህወሀት በውስጥም ደህና ተደርጎ መወቃቱ ቀጥሏል። ሌሊቱን ነጻ የወጡ አከባቢዎችም እንዳሉ መረጃዎች ያመለክታሉ። በጋሸና ጥሩ ተይዟል። የጭፍራው መስመር ለመቀሌ አቀባብሎ እነጉባላፍቶን ይዞ ወደ ወልዲያ እየገሰገሰ ነው። የጋሸናው ድል የህወሀትን ጀሌ ኮምፓሱ የጠፋበት መርከብ አድርጎት ወዲህና ወዲያ እያንከራተተው ነው። በሁሉም ቦታ ተቆርጧል። መግባት እንጂ በህይወት ተርፎ መውጣት ከማይቻልበት ጊዜ ላይ ተደርሷል። ከህወሀት አመራሮች ሰፈር ሾልኮ የሚሰሙ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ህወሀቶች የማርያም መንገድ ስጡንና እንውጣ የሚል ልመና በሹክሹክታ እያሰሙ ነው። አውጥተው አይናገሩት ነገር ደጋፊዎቻቸው ሰማይ ምድሩ ሊደፋባቸው ሆነ። ህወሀቶች የገቡበት ጭንቀትና ቅርቃር በዘራችሁም አይድረስባችሁ የሚያስብል ነው። በድብቅ አማልዱን ዓይነት ጥያቄ ለማቅረብ እየተዘጋጁ ነው ተብሏል።
ረፍዷል። ከህወሀት መወገድ ውጭ ለኢትዮጵያ የሚበጅ ምንም መፍትሄ የለም። ዝግ ነው። ህወሀት የውርደት ሞቱን ጨልጦ፣ ከቆሻሻ ታሪኩ ጋር ከምድር ገጽ ሊጠፋ ይገባል። ከዚህ ውጭ ያለው አማራጭ ኢትዮጵያን ያፈርሳታል። የህወሀት ከጥልቅ ጉድጓድ መግባት ብቻ ነው የኢትዮጵያንም ሆነ የምስራቅ አፍሪካን ሰላምና አንድነት የሚያረጋግጠው። እነሆ ይህ ይሆን ዘንድ ጊዜው ከደጃፋችን ቀርቧል።
እንበርታ!