CNN የኢትዮጵያ መንግስትን ስም የሚያጠፋ ዘገባ ሊሰራ መዘጋጀቱን መንግስት አስታወቀ

CNN የኢትዮጵያ መንግስትን ስም የሚያጠፋ ዘገባ ሊሰራ መዘጋጀቱን መንግስት አስታወቀ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የአሜሪካው የዜና ማሰራጫ CNN በትግራይ ክልል የዘር ማጥፋት እየተፈጸመ መሆኑን የሚያሳይ ሀሰተኛ ዘገባ ለመስራት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ከታማኝ ምንጮች አረጋግጫለሁ ሲል የመንግስት ኮምኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።

እስካሁን ‘የዘር ማጥፋት’ የሚለውን ቃል ሆን ተብሎ ለማዛባት እና ትርጓሜውን ለማዛባት ጥቅም ላይ የዋለ አገላለጽ ቢኖር “የትግራይ ዘር ማጥፋት” የሚለው መሆኑን አገልግሎቱ ህዳር 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታዉቋል።

ይህ የተሳሳተ መረጃ የሕወሓት ኃይል ጥቅምት 25 ቀን 2013 በሰሜን እዝ ሰራዊት ላይ ጥቃት ካደረሰበት ቀን ጀምሮ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ በሕወሓት አማካይነት ሲሰራጭ የነበር መሆኑ በመንግስት ኮምኒኬሽን አገልግሎት ተገልጿል።

ሲ ኤን ኤን የተባለው የዘገባ አዉታር በሕወሓት የሚፈጸሙ አስከፊ ወንጀሎችን በዝምታ ያልፋል ያለው አገልግሎቱ የጋዜጠኝነት ሙያን ከኃላፊነት ስሜት ውጪ መፈጸም ልምድ አድርጎታል ብሏል።

እንደ ሲ ኤን ኤን ያሉ ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ከእዚህ ቀደም ሲያሰራጯቸው የቆዩ የዘር ማጥፋት የሚሉ ዘገባዎች በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ቢሮ ዳሰሳ ውሸት መሆናቸው ተረጋግጧል ሲል መግለጫው አክሏል።

የኢትዮጵያ መንግስት በጦርነቱ ዙሪያ በሚሰራጩ ሀሰተኛ ዘገባዎች ስርጭት ዘመቻ ላይ ያሉ ሁሉንም አካላት በድጋሜ ከተግባራቸው እንዲቆጠቡ ያሳስባል ተብሏል።

LEAVE A REPLY