ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ባለፉት አራት ወራት ብቻ በ63 ህገ ወጥ ድርጅቶች እና በ20 የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያዎች ከ32.5 ቢልየን ብር በላይ በሀሰተኛ ደረሰኝ የተከናወኑ ግብይቶች መፈጸማቸውን የገቢዎች ሚኒስቴር አረጋግጫለሁ አለ።
ህዳር 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ሚኒስቴሩ ከታክስ አስተዳደር ተሰውረው ሲሰሩ የነበሩ 63 ህገ ወጥ ድርጅቶችን እና 20 የሽያጭ መመዝገቢያ/ ካሽ ሬጂስተር ማሽን/ በ4 ወራት ውስጥ መያዙን ይፋ አድርጎ ነበር።
በድርጊቱ ላይ የተሰማሩት ተቋማትና ግለሰቦች 32 ቢልየን 527 ሚልየን 510 ሺህ 503 ብር ዋጋ ያለው ግብይት በሀሰተኛ ደረሰኝ መፈጸማቸውን በሽያጭ መመዝገቢያ ማሽኖቹ ምርመራ ተረጋግጧል ብሏል።
በተመሳሳይ ህጋዊ ደረሰኝ በማይቆርጡ ድርጅቶች ላይ በተደረገ ክትትል 199 ሰዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን በታክስ አስተዳደር አዋጅ ድንጋጌ መሰረት 8 ሚልየን 150 ሺህ ብር አስተዳደራዊ ቅጣት እንዲጣልባቸው መወሰኑን የገቢዎች ሚኒስቴር በይፋዊ የትስስር ገጹ አስታውቋል።