በምስራቅ አፍሪካ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛው ጄፍሪይ ፌልትማን የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ቱርክ እና ግብጽን በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ለማማከር ወደ ሐገራቱ ሊጓዝ ነው ተብሏል።
የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ በሰጡት መግለጫ፤ የልዩ መልዕክተኛው ጉብኝት በኢትዮጵያ በማካሄድ ላይ የሚገኘው ጦርነት መቋጫ እንዲያገኝ የዲፕሎማሲ ድጋፍ ለማጠናከር ያለመ ነው ማለታቸውን ዩ ኤስ ኒውስ ዘግቧል።
ፌልትማን በጉዟቸው ከ3ቱ ሀገራት አቻቸው ጋር ይገናኛሉ የተባለ ሲሆን ጦርነቱ እያደረሰ ያለው ኪሳራ እና በቀጠናው መረጋጋት ላይ የሚያደርሰው ተጽእኖ እንዲቆም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፍላጎት በድርድር ብቻ እንዲጠናቀቅ ነው ሲሉ ኔድ ፕራይስ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ኮምኒኬሽን አገልግሎት በሚሰጣቸው መግለጫዎች ጦርነቱ የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ በመሆኑ በመፍትሄ ሰበብ የሚደረጉ ጣልቃ ገብነቶች ተቀባይነት እንደሌላቸው እያሳሰበ ይገኛል።
ዋሽንግተን አዲስ አበባ ላይ የድህንነት ስጋት እያንዣበበ ነው በማለት በኢትዮጵያ የሚገኙ ዜጎቿ ሀገሪቱን ለቀዉ እንዲወጡ በተደጋጋሚ እየወተወተች እንደምትገኝም የሚታወስ ነው።