ኢትዮጵያ ነገ ዜና ||የሕወሓት ኃይል በአማራ ክልል ጭና እና ቆቦ ከተማዎች የጅምላ ግድያ መፈጸሙን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ተቋም ሂዩማን ራይትስ ዋች ገለጸ።
ተቋሙ እንዳስታወቀው ከነሐሴ 25 እስከ ጳጉሜ 4 2013 ዓ.ም ድረስ በጭና ከተማ በ15 የተለያዩ ጊዜያት 26 እንዲሁም በቆቦ ከተማ በ4 ዙር 23 ንጹሐን ዜጎችን ገድሏል።
ሂዩማን ራይትስ ዋች በመስከረምና ጥቅምት ወራት በአካባቢዎቹ ተገኝቶ የሟች ቤተሰቦችን፣ ነዋሪዎችን፣ የኃይማኖት አባቶችን እና የህክምና ባለሙያዎችን አነጋግሮ በሁለቱ ከተማዎች በድምሩ 49 ሰዎች በሕወሓት መገደላቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል።
ከተጠቀሱት ቀናቶች ዉጪም በጭና እና ቆቦ ከተማ በተፈጸመ ግድያ በጠቅላላ 74 ንጹሐን ነዋሪዎች እንደተገደሉ መረጃ አግኝቻለሁ ሲል ተቋሙ አስታውቋል።
በሰብዓዊ መብት ተቋሙ የግጭትና ጦርነት ጉዳዮች ዳይሬተር ላማ ፋኪህ “በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት በጦር ወንጀል እና በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ያላቸው ተሳትፎ በገለልተኛ አካል መመርመር እንደሚገባው አመላካች ነው” ብለዋል።
ሂዩማን ራይትስ ዋች እስካሁን አለኝ ባለው መረጃ የሕወሓት ኃይል፣ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት፣ የኤርትራ ወታደሮች፣ የአማራ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ አባላት በትግራይና አማራ ክልሎች የጦር ወንጀሎች እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በተለያዩ ደረጃዎች ተፈጽመዋል ብሏል።