ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የአሸባሪው ትሕነግ ወራሪ ኃይል የጠላትነት ጥጉን ባስመሰከረበት ተግባሩ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የአማራ ክልል ሕዝብ የጤና ቀውስ ውስጥ እንዲገባ ማድረጉን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለፀ።
የአማራ ክልል የጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አብዱከሪም መንግሥቱ እንደገለፁት አሸባሪው ትሕነግ የጤና ተቋማትን አውድሟል፡፡ በዚህም ከግማሽ በላይ የሚሆነው የክልሉ ሕዝብ የሚጠቀምበት የጤና መሰረተ ልማት በመዝረፍና በማውደም ጠላትነቱን በተግባር አሳይቷል ብለዋል።
በክልሉ 8 ዞኖች 82 ወረዳዎች የሚገኙ 40 ሆስፒታሎች፣ 453 ጤና ጣቢያዎች፣ 1 ሺሕ 850 ጤና ኬላዎች፣ 4 የደም ባንኮች እንዲሁም 1 ኦክስጅን ማምረቻ ማዕከል በአጠቃላይ 2 ሺሕ 348 የጤና ተቋማት በሽብር ቡድኑ መውደሙን ምክትል ኃላፊው ለዋልታ ተናግረዋል።
በክልሉ በተገነቡ የጤና መሠረተ ልማቶች ላይ የሽብር ቡድኑ በወረራቸው አካባቢዎች ያደረሰውን መጠነ ሰፊ ዘረፋና ውድመት የዓለም ጤና ድርጅትም ሆነ የሚመለከታቸው ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እስካሁን ለማየትም ሆነ ለመደገፍ ፍላጎት አላሳዩም ብለዋል፡፡
የጤና መሰረተ ልማት በወደመባቸው አካባቢዎች የህክምና አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ባለሃብቶች የሚመለከታቸው አካለትና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።