ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የተባበሩት መንግሥታት የሰብኣዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ላይ ልዩ ስብሰባ እንዲጠራ ከፈረሙ 52 አገራት ውስጥ አንድም አፍሪካዊ አገር አለመኖሩ ታወቀ፡፡
ይህም ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ የሚለው እሳቤ እንዲሁም የ”በቃ” #Nomore ንቅናቄ ፍሬ እያፈራ የመሆኑ አንዱ ማሳያ መሆኑ እየተጠቀሰ ነው፡፡
አሜሪካና ተባባሪዎቿ በህወሀት ተንኳሽነት በሰሜኑ ክፍል በተቀሰቀሰው ጦርነት ላይ የሰብአዊ ጥሰቶች ተፈጽመዋል በሚል ምክንያት መላ አፍሪካን ለማንበርከክ የሚያደረጉትን ጥረት አሁንም መቀጠላቸው ተመልክቷል።
የሰብኣዊ መብት ጥምር ምርመራ ሪፖርት ጥቅምት 24 ለሕዝብ ይፋ በሆነበት እና የኢትዮጵያ መንግሥትም በሪፖርቱ የተመላከቱ ምክረ ሐሳቦችን ተቀብሎ ወደ ተጨባጭ ተግባር በገባበት በአሁኑ ወቅት አሜሪካ በአፍሪካ ላይ ያላትን የጂኦ ፖለቲካ ፍላጎት ለማስፈፀም የሰብኣዊ መብቶች ምክር ቤቱ በድጋሚ ስብሰባ እንዲጠራ 52 ሀገራት ፊርማ አስገብተዋል።
ሆኖም ፊርማውን ከፈረሙት 17 የምክር ቤቱ አባላትና 35 ታዛቢ አገራት ውስጥ አንድም አፍሪካዊ አገር አለመኖሩ ታውቋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የተወሰኑ አባል አገራት ለፖለቲካዊ ዓላማ ሲሉ የመንግሥትን ጥረት በመናቅ ልዩ ስብሰባ እንዲደረግ መጠየቃቸው ግራ የሚያጋባና የሚያበሳጭ እንደሆነ አሳውቋል፡፡
የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጰያ ላይ በተደጋጋሚ ጫና ሲታደርግ እንደነበር የሚታወሥ ሲሆን አዲስ አበባ የጦርነት ቀጠና ትሆናለች በሚል ዜጎቿ እንዲወጡ ያልተሳካ ውትወታ ስታደርግ መቆየቷ አይዘነጋም።