ኢትዮጵያ ነገ ዜና || አሸባሪው ህወሐት በወረራ ይዟቸው በነበረባቸው አካባቢዎች ያደረሰውን ውድመት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በዝምታ ማለፉ አሳዛኝ ነው ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለፁ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንን ጨምሮ አንድ አንድ ምዕራባውያን አገራት የሽብር ቡድኑ ያደረሰውን ውድመት ከመናገር መቆጠባቸውን አስታውቀዋል።
አምባሳደር ዲና እንዳሉት፤ አሸባሪው የህወሐት ቡድን በወረራ ይዟቸው በነበሩት የአማራና የአፋር ክልሎች በርካታ ውድመት ፈጽሟል። ስምንት ነጥብ ሶስት ሚሊየን ዜጎች ለከፋ ችግር እንዲጋለጡ አድርጓል። ሆኖም ይህን በግልጽ የሚያውቁ የውጭ ሀይሎች ጥፋቱን በዝምታ እያለፉት ይገኛሉ።
አሸባሪው ቡድን ያደረሰውን ውድመት መናገር ሲኖርባቸው እነርሱ ግን ዛሬም ድረስ ዜጎቻቸው ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ጥሪ በማድረግ ላይ ይገኛሉ ብለዋል። ይህም መንግስትን እንዳሳዘነ ገልጸዋል።
በቀጣይ የውጭ መገናኛ ብዙኃን ሽብርተኛው ቡድን ያደረሰውን ውድመት በስፍራው ተገኝተው እንዲዘግቡ መንግስት ሁኔታዎችን እንደሚያመቻችም አምባሳደሩ ጠቁመዋል።