ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ የት እንደታሰረ የሚነግራቸው አካል ባለማግኘታቸው ጭንቀት ላይ መሆናቸውን ባለቤቱ ወይዘሮ ሰላም በላይ ተናግረዋል፡፡
ጋዜጠኛው ባለፈው አርብ ዕለት ወደ ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ከተወሰደ በኋላ ቤተሰቦቹ ወደዚያው አቅንተው ለማየት ቢጠይቁም የታሰረበትን ትክክለኛ ቦታ የሚነግራቸው እንዳጡ መናገራቸው ይታወሳል።
ጉዳዩን የያዘው የኦሮሚያ ፖሊስ ነው በመባሉ ቤተሰቦቹ 6 ኪሎ ወደሚገኘው የኦሮሚያ ፖሊስ መምሪያ ቀጥሎም ግሎባል አካባቢ ወደሚገኘው የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ሄደው ቢጠይቁም ሁለቱም ቦታዎች ታምራት እንደሌለ ነው የተነገራቸው።
ይልቁንም ወደ ቡራዩና ገላን ከተሞች ሄዳችሁ አጣሩ የተባሉት የታምራት ቤተሰቦች በቡራዩ ከተማ በሚገኙ ሶስት ፖሊስ ጣቢያዎችና በተጨማሪም ገላን ኮንዶሚኒየም ወደ ሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ በተደተጋጋሚ ቢያቀኑም ማግኘት እንዳልቻሉ ተናግረው ነበር ።
በዚህም ጋዜጠኛ ታምራት የታሰረበትን ቦታ ባለማግኘታቸው መድሃኒትና ምግብ እንኳን ማድረስ እንዳልቻሉና በዚህም የተነሳ ከፍተኛ የሆነ ጭንቀት ውስጥ እንደሚገኙ ባለቤቱ ገልፀዋል።
ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ቀደም ባለው ጊዜ የአዲስ ነገር ጋዜጣ ባልደረባ የነበረ ሲሆን በስራው ምክንያትም ከሀገር እንዲሰደድ ተገዶ በአሜሪካ መቆየቱ ይታወሳል። ባለፈው አርብ ከጠዋቱ 4 ሰዓት 30 ላይ “ለጥያቄ ትፈለጋለህ” በሚል ከመኖሪያ ቤቱ መወሰዱ አይዘነጋም፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር መንግስት የታሰሩትን ጋዜጠኞች ፍትህ የማግኘት መብት እንዲያከብር ባወጣዉ መግለጫ ጠይቋል፡፡