ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በአንጸባራቂ ድል ወደፊት እየገሠገሡ የሚገኙት ጀግኖቹ የመከላከያ ሠራዊትና የአማራ የጸጥታ ኃይሎች አብዛኞቹን የዋግ ኅምራ አካባቢዎች ነጻ በማውጣት የዞኑን ዋና ከተማ ሰቆጣን ተቆጣጥረዋል።
አካባቢው ከአሸባሪው ሕወሓት ነጻ በሚወጣበት ጊዜ የዋግ ኅምራ ሚሊሻዎች አስደናቂ ጀብዱ የፈጸሙ ሲሆን፣ የአካባቢው ሕዝብም ከመከላከያ ሠራዊትና ከአማራ ክልል የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመጣመር ደጀንነቱን በብቃት አሳይቷል።
የመከላከያ ሠራዊትና የአማራ የጸጥታ ኃይሎች ቀሪዎቹን ሥፍራዎች እያጸዱ፣ የፈረጠጠውን የአሸባሪውን ጀሌ እየደመሰሱ፣ ወደ አበርገሌ በመገሥገሥ ላይ ይገኛሉ።
በተያያዘም ጀግኖቹ የመከላከያ ሠራዊትና የአማራ ክልል የጸጥታ ኃይሎች፣ በቆቦ ግንባር በአንድ በኩል ሙጃና ጥሙጋ ላይ የሠፈረውን የጠላት ኃይል በመጥረግ ወደ አላማጣ ከተማን የተቆጣጠሩ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ተኩለሽን ተቆጣጥረው በማጽዳት፣ ወደ መረዋና ኮረም እየገሠገሡ እንደሚገኝ የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
በእሳታማው የጀግኖች ክንድ የተደቆሰው አሸባሪው ሕወሓት፣ ተቸካይና ኋላ ቀር በሆነ የጦር ዘይቤ፣ ዕብሪትን እንደ መሣሪያ በመጠቀም፣ ከገባባቸው የአማራና የአፋር ክልል አካባቢዎች እንደገባ መውጣት አቅቶት፣ ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሣራ ደርሶበት ተደመስሷል።