ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ከሰኔ ወር 2013 ዓ.ም ወዲህ በሕወሓት የሽብር ቡድን የተፈፀሙ ወንጀሎችን የማጣራት ስራው መጀመሩን የፍትህ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በፍትህ ሚኒስቴር የሚመሩ የወንጀል ምርመራ እና ማስቀጣት ቡድኖች በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በሕወሓት አሸባሪ ቡድን የተፈፀሙትን ወንጀሎች በማጣራት አጥፊዎችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችለውን የወንጀል ምርመራ ወንጀሎቹ በተፈጸሙበት አካባቢዎች በመገኘት መጀመራቸውንም ሚኒስቴሩ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ገልጿል።
የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን ህገ ወጥ ድርጊት ቀጥሎ በወረራቸው እና በአሁኑ ወቅት በሀገር መከላከያ ሰራዊትና በሌሎች ጥምር የፀጥታ ኃይሎች ወታደራዊ እርምጃ ነፃ በወጡ የአፋርና አማራ ክልሎች የተለያዩ ቡድኖችንና ንኡሳን ቡድኖችን በማዋቀር ወደ አካባቢው በመላክ የወንጀል ምርመራ ስራቸውን እንዲጀምሩ መደረጉም ተገልጿል።
የሽብር ቡድኑ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል መጠነ ሰፊ ወረራ በማካሄድ የዓለም ዐቀፍ ስምምነቶችን እና የሀገሪቱን ህግጋቶች በመጣስ በሰላማዊ ሕዝብ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ሲፈፅም በነበረባቸው የአማራና የአፋር አካባቢዎች በሙሉ ከፍትህ ሚኒስቴር፣ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከክልል ፖሊስና ከክልል ፍትህ ቢሮዎች እንዲሁም ሌሎች አጋዥ ኃይሎች የተውጣጡ አካላት የተሳተፉበት ቡድን በማዋቀር የምርመራ ስራው እንዲጀመር አድርጓል።