ኢትዮጵያ ነገ ዜና || አፍሪካዊያን በኢትዮጵያ ላይ የሚፈጸምን ማንኛውንም ጥቃት አፍሪካ ላይ የተቃጣ አድርገን እንቆጥረዋለን ሲሉ ኡጋንዳዊው ፓን አፍሪካኒስት ሩጋራማ ዳንኤል ገለጹ።
እኛ አፍሪካዊያን በኢትዮጵያ ላይ የሚደርስን ማንኛውንም ጥቃት አፍሪካ ላይ እንደተቃጣ አድርገን እንቆጥረዋለን” ይላሉ የኡጋንዳ ብሔራዊ የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ሊቀ መንበር ዶክተር ሩጋራማ ዳንኤል ገለጹ።
አፍሪካዊያን የምዕራቡ ዓለም አገራት በአፍሪካ ላይ መጫን የሚፈልጉትን የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ እምቢተኝነታቸውን በማሰማት ትግል ማድረግ አለባቸውም ብለዋል።
የኡጋንዳ ብሔራዊ የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ሊቀመንበር ዶክተር ሩጋራማ ዳንኤል ÷ ኢትዮጵያ በአፍሪካዊያንና በጥቁር ሕዝቦች ዘንድ ትልቅ ቦታ እንዳላት ለኢዜአ ገልጸዋል።
የአፍሪካ አገራት በቅኝ ግዛት ውስጥ በነበሩበት ወቅት ኢትዮጵያ “ነጻነቴን አሳልፌ አልሰጥም” በማለት ባደረገችው ትግል ሉዓላዊነቷን ማስከበር እንደቻለች አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ነጻነቷን ለማስጠበቅ ያደረገችው ትግል ለአፍሪካዊያንና ለጥቁር ሕዝቦች ብርታት እንደሰጠና ከጭቆና ለመላቀቅ የተደረገውን እንቅስቃሴ እንዳቀጣጠለ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያ እየተዋጋች ያለችው የውስጥ ጠላቶቿን ብቻ ሳይሆን በእጅ አዙር በአፍሪካ ላይ የቅኝ ግዛት እሳቤን መጫን ከሚሹ ሃይሎች ጋር እንደሆነም አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ በግልጽ የማይታዩ ነገር ግን ከጀርባ ሆነው ኢትዮጵያን በማዳከም አፍሪካን ለማዳከም ከሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ጋር እየታገለች ነው፤ ለዚህም ነው ኢትዮጵያ የአፍሪካን ጦርነት እየተዋጋች ነው የምንለው ብለዋል ።