በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ አረቢያ እስር ስቃይ ላይ ናቸው 

በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ አረቢያ እስር ስቃይ ላይ ናቸው 

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በሳዑዲ እስር ቤት እየተሰቃዩ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ግፋቸውን ህዝብ እንዲሰማላቸውና የሚመለከተው አካል መፍትሄ እንዲሰጣቸው ተማፀኑ።

ለበርካታ ወራት በአሰቃቂ ሁኔታ በእስር ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያውኑ ያሉበት ሁኔታ ተስፋ አስቆራጭ መሆኑን ገልፀዋል።

በእስር ቤቱ በርካታ ቁጥር ያለው እስረኛ እንደሚገኝ የገለፁት ታሳሪዎቹ ከነዚህ ታሳሪዎች ውስጥ አቅመ ደካሞችና ሴቶች እንዲሁም ህፃናት ሳይቀር እንደሚገኙበት አሳውቀዋል።

አሁን ላይ ትኩረት የሚሰጣቸውን አካል በማጣታቸው እንግልቱ መጨመሩንና ተስፋቸው መሟጠጡን በመግለፅ ለህዝብና ለመንግስት አቤት እያሉ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

እስር ቤቱ ደረጃውን ያልጠበቀና እስር ቤት ሊባል የማይችል ማጎሪያ እንደሆነ የገለፁት ታሳሪዎቹ በታሰሩ ወቅት የለበሱትን ልብስ ብቻ እንደለበሱ አመታትን ሳይቀር ሊያሳልፉ የሚችሉበት ዘግናኝ ቦታ መሆኑን ጨምረው ገልፀዋል።
ይህን አስከፊ ሁኔታ በመመልከት የሚመለከተው አካል መፍትሄ ይሰጣቸው ዘንድ ተማጽነዋል።
ሳዑዲ አረቢያ እስር ላይ ሚገኙ ወገኖች ባስተላለፉት መልዕክት ” አንድ ነጭ በሌላ ሀገር ቢታሰር የዓለም ሚዲያዎች እያብጠለጠሉ ቢያስወሩት ነጩ ተፈቷል ይባላል ፤ እኛ ግን በመቶ ሺዎች የምንቆጠር ኢትዮጵያውያን መብታችን የአንድ ነጭ ያህል እንኳን አልሆነም ” ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ተቆርቋሪ ነን የሚሉት አካላት በማያገባቸው ነገር በየሀገሩ የሚዳክሩ ለምን ወደ ሳዑዲ ጎራ አይሉም፤ ለምን መጥተው እስር ቤቱን አይጎበኙም እስር ቤቶች በኢትዮጵያውያን እና በሌሎችም ሀገራት ዜጎች ተጨናንቋል በተለይ በኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርደው ስቃይ የከፋ ነው ሲሉ ወቅሰዋል።

LEAVE A REPLY