ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በጦርነትና በግጭት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች መልሶ ማቋቋሚያ የሚውል የአምስት ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት መዘጋጀቱን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ ገለጹ፡፡
በገንዘብ ሚኒስቴር የሚመራው የመልሶ ማቋቋም ሴክሬታሪያት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የመጀመሪያውን ውይይት ተደርጓል፡፡
በወቅቱ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ በሚኒስቴሩ የተዘጋጀው የአምስት ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡን ጠቁመው ተጨማሪውን በጀት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዳጸደቀው በቀጥታ ወደ ስራ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
መንግሥት ከሚመድበው መነሻ በጀት በተጨማሪም ከልማት አጋሮች በተለይም ከዓለም ባንክ ለመልሶ ማቋቋሙ ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚጠበቅና የመልሶ ማቋቋሙ መርኃ ግብሩ በመንግሥት የሚመራ፣ የተቀናጀ፣ በየደረጃው በፕሮግራም ተግባራዊ የሚደረግ፣ ተጠያቂነት ያለውና ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የሚተጋ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
የመልሶ ማቋቋም መርኃግብሩ ከሰሜኑ እና በሌሎች የአገሪቱ ክልሎች በግጭት የተፈናቀሉትንም እንዲያካትት፣ የሀብት አሰባሰብ ድግግሞሽ እንዲወገድና በአንድ ቋት እንዲሰባሰብ፣ ክልሎች ንቁ ተሳትፎ የሚደርጉቡት ምቹ ሁኔታ እንዲመቻች፣ ከሌሎች መሰል ብሔራዊ ኮሚቴዎች ጋር በቅንጅት እንዲሰራና የግሉን ዘርፍና ዲያስፖራውን እንዲያሳትፉ የኮሚቴው አባላት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
በውይይቱ የኮሚቴው አባላት የሆኑት የትምህርት፣ የጤና፣ የፕላንና ልማት፣ የውሃና ኢነርጂ፣ የኢንዱስትሪ፣ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ፣ የሥራና ክህሎት፣ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሮችና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌዴራል መስሪያ ቤት አመራሮች ተሳታፊ መሆናቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡