ኢትዮጵያ ነገ ዜና || አሜሪካ የኢትዮጵያ ጦርነት እንዲያበቃ ከፈለገች አሸባሪውን ትሕነግ ከመደገፍ ልትቆጠብና እውነተኛ የሰላም እገዛን ልታደርግ እንደሚገባ ፕሮፌሰሯ አን ፊትዝ ጌራልድ እና ተመራማሪው ብሮንውይን በሩቶን ጠየቁ፡፡
የባዚል ስኩል ኦፍ ኢንተርናሽናል አፌርስ ዳይሬክተርና የዊልፍሪድ ላውሬር ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሯ አን ፊትዝ ጌራልድ እና በአትላንቲክ ካውንስል የአፍሪካ ማዕከል የረጅም ጊዜ ልምድ ባለቤት የሆኑት ተመራማሪው ብሮንውይን በሩቶን ‹የኢትዮጵያ ጦርነት እንዲያበቃ ባይደን በኢትዮጵያ ላይ የያዘውን የተዛባ አቋም ሊቀይር ይገባል› በሚል ርዕሰ ጉዳይ ሰፊ ሐተታን በፎሬይን ፖሊሲ ላይ አስነብበዋል፡፡
ጸሐፊዎቹ በትሕነግ አመራሮች ይሁንታም ጭምር ድጋፍ አግኝተው በመጋቢት 2010 ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት የመጡት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኤርትራ ጋር ጭምር ሰላም በመፍጠር አገሪቱን ወደተሻለ ምዕራፍ ለማሻገር አስበው ሲሰሩ ትሕነግ ግን ሁሉን በመቃወም ለጦርነት ይዘጋጅ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ትሕነግ ጦርነቱን በጀመረ ጥቅምት 30/2013 በተጠና መልኩ በአማራ ተወላጆች ላይ በማይካድራ ዘርን የማፅዳት ግድያን በመፈጸም ‹በመቶዎች የሚቆጠሩ ንፁሃንን በብሔር ማንነታቸው መክንያት መጨፍጨፉን ግልጽ አድርገዋ።
ስለሆነም የኢትዮጵያ ጦርነት እንዲቆም የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ትሕነግን ከመደገፍ ሊታቀብና የያዘውን ስህተት ላይ የቆመ አቋም ቀይሮ ከኢትዮጵያዊያን እውነት ጎን ሊቆም በተግባርም የሰላም ደጋፊነቱን ሊያሳይ እንጂ ማዕቀብ በመጫን ድብቅ ፍላጎቱን ሊያሳካ አይገባውም ሲሉ ሞግተዋል።

























