22 የፖለቲካ ፓርቲዎች በአማራና አፋር ክልሎች የወደሙ አራት ተቋማትን ሊረዱ ነው

22 የፖለቲካ ፓርቲዎች በአማራና አፋር ክልሎች የወደሙ አራት ተቋማትን ሊረዱ ነው

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || አገር ከፖለቲካ ልዩነት እና ከፓርቲ በላይ ነው በሚል መርህ 22 የፖለቲካ ፓርቲዎች በአማራና አፋር ክልሎች የወደሙ አራት የማህበራዊ ተቋማትን ሊገነቡ መሆኑን ተገለፀ።

 በአዲስ አበባ የሚንቀሳቀሱ 22 የፖለቲካ ፓርቲዎች በአማራ እና አፋር ክልሎች የወደሙ አራት የማህበራዊ ተቋማትን ሊገነቡ መሆኑን የፓርቲዎች ጥምረት ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አስታወቀ።

በእያንዳንዱ ዘርፍ ኮሚቴ አዋቅሮ የወገንን ሃይል ሲደግፍ መቆየቱን የጥምረቱ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ እና የኢሕአፓ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ መጋቢ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በደሴ ግንባር በመገኘት ከ18 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ቁሳቁስ ድጋፍ ለወገን ጥምር ጦር ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው ቀጣዩ ግንባር ደግሞ ኢትዮጵያን ለምጣኔ ሀብታዊ ጉዳት ከዳረገው ጦርነት በምታገግምበት አማራጮች ላይ መሳተፍ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሸባሪው የሕወሃት ወራሪ ሃይል በከፍተኛ ደረጃ የወደመው ተቋማትን መልሶ መገንባት እና በጦርነቱ ተፈናቅለው ለማህበራዊ ቀውስ የተዳረጉ ወገኖችን መደገፍ ቅድሚያ ይሰጠዋል ብለዋል።

በዚህም በመዲናዋ የሚንቀሳቀሱ 22 ፓርቲዎች ጥምረት በአማራና አፋር ክልሎች በእያንዳንዳቸው አንድ ሆስፒታልና አንድ ትምህርት ቤት በድምሩ አራት ተቋማትን ሊያስገነባ መወሰኑን ገልጸዋል።

ፓርቲዎቹ አገር ከፖለቲካ ልዩነት እና ከፓርቲ በላይ ነው በሚል መርህ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ጠቅሰው ይህም ኢትዮጵያ እንደ አገር የገጠማትን ችግር እንድትሻገር ጉልህ ሚና አለው ነው ያሉት።

ከአገራዊ ለውጡ በኋላ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደበፊቱ አማራጭ ሀሳብ የሌላቸው የይስሙላ ፓርቲ ስብስብ ሳይሆኑ የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋትና ለአገር የሚቆረቆሩ መሆናቸውን ማሳያ ነው ብለዋል።

LEAVE A REPLY