ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በአዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የገላን ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ከ14 ቀን በፊት ጋዜጠኛ ታምራት ነገራን ለዛሬ ታህሳስ 21፣ 2014 መቅጠሩ የሚታወስ ሲሆን በዛሬው ዕለት በዋለው ችሎት የጋዜጠኛ ታምራት ነገራ የምርመራ መዝገብ ተዘግቶ ከዚህ በኋላ ጉዳዩን የሚከታተለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሆኑም ታውቋል።
የጋዜጠኛው ጠበቃ የደንበኛቸው የዋስ መብት እንዲጠበቅ ጠይቀው ፍርድ ቤቱም የተጠየቀውን የዋስ መብት ፋይል መክፈት እንዲችል ፈቅዶ የምርመራ መዝገቡን መዝጋቱን ተራራ ኔትወርክ ዘግቧል።
የተራራ ኔትዎርክ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ተላልፎ በኦሮሚያ ክልል ገላን ከተማ ፖሊስ መምሪያ ከታህሳስ 1፣ 2014 ጀምሮ በእስር ላይ እንደሚገኝ ይታወሳል።
ጋዜጠኛው ከቤቱ ከተወሰደ የመጀመሪያዎቹ 7 ቀናት የት እንዳለ ሳይታወቅ ቆይቶ ከ7 ቀን በኋላ ፍርድ ቤት መቅረቡ ይታወሳል።
ይሁን እንጅ ጋዜጠኛ ታምራት መጀመሪያ ወደ ሶስተኛ ፖሊስ ቢወሰድም ከፌደራል ፖሊስ ወደ ኦሮሚያ ፖሊስ እንደተዘዋወረም ታውቋል።

























