ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ዲያስፖራው የኢንተርኔት ግንኙነት በሌለበት ቦታ የዲጂታል ትምህርት መስጠት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ለሙከራ ይዘው መጡ።
ከ40 ዓመት በላይ አሜሪካን አገር የኖሩት ሚደቅሳ በየነ የኢንተርኔት ግንኙነት በሌለበት ቦታ የዲጂታል ትምህርት መስጠት የሚያስችል መሳሪያ ለሙከራ ለአገራቸው ይዘው መጥዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ወደ አገር ቤት መመለስ ጥሪን ተቀብለው ወደ አገራቸው የመጡ ትውልደ ኢትዮጵያዊው ሚደቅሳ ወደ አገር ሲመጡ የኢንተርኔት ግንኙነት የሌላቸው ትምህርት ቤቶችን ሊጠቅም የሚችል ቴክኖሎጂ ይዘው እንደመጡ ተናግረዋል።
ቴክኖሎጂው በሶላር ኃይል የሚሰራ፣ የራሱ ዋይፋይ ያለውና ተንቀሳቃሽ 2 ቴራባይት ሰርቨር የያዘ ሲሆን ከኮምፒውተርና ከሞባይል ጋር በማገናኘት የመማሪያ መሳሪያዎችን ማግኘት የሚቻልበት ነው ተብሏል።
ቴክኖሎጂው የተለያዩ የትምህርት አይነቶች የያዙ መጽሐፍት፣ መርጃ መጽሐፍት፣ ሌክቸሮች እና ቪዲዮዎች፣ ጥናታዊ ጽሑፎች፣ ንግግሮች፣ መዝናኛዎች እና በሺዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ማስረጃዎችንም የሚይዝ መሆኑ ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመልክቷል።
ከ60 ሺህ በላይ መጽሐፍትን የያዘው ሥርዓቱ መጽሐፍቶቹን በማንኛውም ጊዜ በነፃ ማውረድም የሚስችል ነው ተብሏል።
በአሁን ሰዓት መሳሪያውን በአገር ውስጥ ለመጠቀም እንዲቻል የትምህርት ሚኒስቴር የአይሲቲ ባለሙያዎች እንዲገመግሙት እየተደረገ ነው ተብሏል።

























