የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የአገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮችን የመጠቆሚያ ጊዜው እንዲራዘም ጠየቁ

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የአገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮችን የመጠቆሚያ ጊዜው እንዲራዘም ጠየቁ

Federal Democratic Republic of Ethiopia - vector map

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በሀገር ዉሰጥ የሚንቀሳቅሱ 11 አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮችን የመጠቆሚያ ጊዜው እንዲራዘምና የመጨረሻዎቹ ዕጩዎች ከተጠቆሙት ሰዎች መሐከል ተለይተው የሚቀርቡበት መመዘኛ ግልጽነት እንዲኖረው ጠየቁ።

ድርጅቶቹ በዛሬዉ እለት ባሰራጩት መግለጫ አገራዊ ምክክሩን የሚያመቻቸው ኮሚሽን ተዓማኒነቱ ጥያቄ ውስጥ እንዳይገባ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል በማለት የኮሚሽነሮች ጥቆማ ከሕዝብ፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ እንዲሁም ከፖለቲካ ፓርቲዎች እየተሰበሰበ መሆኑ ሊደነቅ የሚገባው ቢሆንም፥ የተሰጠው ጊዜ ግን አጭር ሆኖ አግኝተነዋል ብለዋል በተጨማሪም፣ በሕዝብ ከተጠቆሙ ኮሚሽነሮች መካከል የመጨረሻ 14ቱ ዕጩዎች በአፈ ጉባዔው ተለይተው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚቀርቡ የተገለጸ ሲሆን፥ ዕጩዎቹ ተለይተው የሚቀርቡበትን መመዘኛ ሁኔታ በተመለከተ የአሠራር ግልጽነት አለመኖሩን አስተውለናል።

በሕዝብ የተጠቆሙት ዕጩዎች በምን መመዘኛ እንደተመረጡ ለብዙኃን ግልጽ ማድረግ የሚቻልበትን አሠራር መመሥረት ለኮሚሽኑ ተዓማኒነት ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለን እናምናለን።በቅርቡ የፀደቀው የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚያመቻቸው የምክክር ሒደት ሁሉን አካታች፣ ተዓማኒ እና ግልጽ መሆኑን ለመከታተል የበኩላችንን ለመወጣት ቅድመ ዝግጅት እያደረግን እንገኛለን ብለዋል ድርጅቶቹ በመግለጫቸዉ።

ጥያቄውን ያቀረቡት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መካከል፣
የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ህብረት፣
የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል፣
ኢስት አፍሪካን ኢኒሺዬትቭ ፎር ቼንጅ፣
የሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች
የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር
የኢትዮጵያ አርታኢያን ማኅበር ፣
ሴታዊት ንቅናቄ ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ፣
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል፣
ፕሮፌሰርመስፍንወልደማርያም ፋውንዴሽን፣ እና
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶችጉባዔ ናቸዉ።

LEAVE A REPLY