ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ከጆ ባይደን ጋር ያደረጉት ውይይት በዲፕሎማሲው መሻሻሎች የመኖራቸው ማሳያ...

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ከጆ ባይደን ጋር ያደረጉት ውይይት በዲፕሎማሲው መሻሻሎች የመኖራቸው ማሳያ ነው ተባለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ ሳምንታዊ መግለጫቸውን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሰጥተዋል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ጋር ያደረጉት የስልክ ውይይት ከዚህ ቀደም የነበረው የግንኙነት መንፈስ እየተቀየረ ለመሆኑ ማሳያ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህግ ማስከበሩ ዘመቻ ዙሪያ ለፕሬዚዳንቱ እንዳብራሩ የገለፁት አምባሳደር ዲና የሰብአዊ መብት አያያዝ ፣ የሰብአዊ ድጋፍ ማቅረብ እና በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ማቋቋም ጋር የተገናኙ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን አንስተዋል።

ከዚህ ቀደም የተስተዋለውን በጥርጣሬ የተቃኘ አካሄድ ለመለወጥ ለንግግር ዝግጁ መሆናቸውን ማሳየታቸውንና በጋራ ጉዳዮች ላይ አብረው ለመስራት መስማማታቸውን ነው ያመለከቱት።

በዚህም የፓለቲካ ዲፕሎማሲ ምህዳሩ መንፈስ እየተቀየረ መምጣቱ ታይቷልም ብለዋል፡፡ ግንኙነትን በማጠናከር ረገድም ውጤታማ ስራ እንዲሰራ መንገድ የሚፈጥር መሆኑን አንስተዋል።

በአንድ በኩል የህልውና አደጋውን ለመቀልበስ በተደረገው ዘመቻ የተገኘው ድል፣ በሌላ በኩል ብሄራዊ መግባባትን ለማምጣት የተጀመረው ሂደት በኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የበረታ ትግል የእስካሁኑ ጫና ትርጉም ያጣ እንዲሆን አድርገዋል ብለዋል።

ጫናው ሙሉ በሙሉ ተቀርፏል ባይባልም በተሰሩ ስራዎች ጫናዎቹ ዋጋ እንዲያጡ እና ትርጉም እንዳይኖራቸው ያደረገ መሆኑን በመግለጫቸው አንስተዋል። ለዚህም ከዚህ ቀደም የጉዞ ማስጠንቀቂያዎችን ሲሰጡ የነበሩ አሁን መንፈሱ እየተቀየረ በመምጣቱ ያንን ከማድረግ እየተቆጠቡ ነው ብለዋል።

LEAVE A REPLY