ኢራን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ  ጣልቃ ገብነት እንደምትቃወም አስታወቀች

ኢራን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ  ጣልቃ ገብነት እንደምትቃወም አስታወቀች

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ኢራን አንዳንድ የምዕራባዊያን አገራት በሰብዓዊ መብት ስም ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች አገራት የውስጥ ጉዳይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት በጽኑ እንደምትቃወም በኢትዮጵያ የኢራን አምባሳደር ሰመድ አሊ ላኪዛዴህ ገለጹ፡፡

አምባሳደሩ ሰብዓዊ እሴቶች ለሁላችንም ዋጋ ያላቸው ሃብቶች በመሆናቸው የምዕራባዊያንን ጣልቃ የመግባት ፍላጎት ለማሟላትና ለእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ማስፈጸሚያ ሲባል መሸርሸር የለባቸውም ብለዋል፡፡

በዚህም አንዳንድ ምዕራባዊያን አገራት ሰብዓዊነት የሚሉትን ተረክ በማንሳት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉት ጫና ህገ ወጥና ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ጠቅሰው ኢራን ይህንን ድርጊት እንደምትቃወም ተናግረዋል፡፡
አገራቱ ጠንካራ፣ ነጻና ሉዓላዊነቷ የተከበረ ኢትዮጵያን ማየት ስለማይፈልጉ ሰብዓዊ ጥሰቶችን በመጥቀስ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እያደረጉ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት በቅኝ አገዛዝ ስር ያልወደቀች ብቸኛ ሀገር መሆኗን ያስታወሱት አምባሳደሩ የኢትዮጵያ ነጻነት በመላው ዓለም የጸረ-ቅኝ አገዛዝ ንቅናቄን በማነሳሳት ይታወቃል ብለዋል፡፡
የምዕራባዊያን አገራት ላለፉት 42 ዓመታት በኢራን ላይ ሁሉንም አይነት ጫና ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸው ከዚህ አኳያ “ሰብዓዊ መብት” በማለት በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉት ያለውን ጣልቃ ገብነት ኢራን ትገነዘባለች ሲሉም አክለዋል፡፡

የምዕራባዊያን ጣልቃገብነት ሊቢያ፣ ሶሪያ፣ የመን፣ አፍጋኒስታንና ሌሎች መሰል አገራትን ለከፋ ቀውስ መዳረጉንም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የምዕራባዊያኑን ጫናና ጣልቃ ገብነት በመቃወም የምታደርገው ትግል በርካታ አፍሪካዊያን የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝን እንዲታገሉ እንደሚያነሳሳ አብራርተዋል፡፡

LEAVE A REPLY