ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በአፋር ክልል ፣ አብአላ ከተማ በሚሰነዘር የከባድ መሳሪያ ድብደባ የከተማው ነዋሪ ከቄዬው እየተሰደደ መሆኑን የከተማው ከንቲባ ተናገሩ።
አብአላ ከተማ ከንቲባ ጣሂር ሀሰን ለቪኦኤ ሬድዮ ጣቢያ እንደተናገሩ ከመቀሌ ከተማ 40 ኪ/ሜ ርቀት ላይ የምትገኘው የአፋር የንግድ ከተማ አብአላ ህወሓት ተቆጣጥሯቸው ከነበሩት የአፋር እና አማራ ክልሎች እንዲወጣ ከተደረገ በኋላ አብአላ ላይ ተደጋጋሚ ጉዳት ደርሷል ብለዋል።
የከተማው ከንቲባ ” አሁንም ድረስ አላቋረጠም ንፁሃን መደብደብ፤ በከባድ መሳሪያ መደብደብ እስካሁን አላቆመም፤ በእግረኛም ወረራ እየሞከረ ነው ብለዋል።
መጀመሪያውንም እንደሚታወቀው በየአካባቢው የሚያደርገውን ወረራ እና የንፁሃን ጭፍጨፋ ሙከራ ነው ያደረገው ያኔም አልተሳካለትም እስካሁን አላቋረጠም።
በከባድ መሳሪያ ንፁሃንን እየደበደበ ነው፤ በእግረኛም እየሞከረ ነው ዘረፋ ለማድረግም እየሞከረ ነው ቢሆንም ግን አልተሳካለትም። ወደላይ ተመልሷል እስካሁን ግን የቆመ ነገር የለም፤ ከከተማው ራቅ ብሎ ከባድ መሳሪያ እየተኮሰ ነው ” ብለዋል።
እየተፈፀመ በሚገኘው ጥቃት ከንፁሃን በተጨማሪ የአምልኮ ቦታዎች ፣ የመንግስት እና የግል ባለሀብቶች ንብረት ላይ ጉዳት መደረሱ ተገልጿል።
የደረሰውን ጉዳት በቁጥር ደረጃ ለመግለፅ ጥናት እየተደረገ መሆኑን የአብአላ ከንቲባ ተናግረዋል።

























