ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የታዋቂዎቹ የሆሊዉድ ተዋንያን አንጀሊና ጆሊ እና ብራድ ፒት ፋውንዴሽን 2 ሚሊየን ዶላር የሚያወጣ በሳምባ ነቀርሳና ኤች አይ ቪ የተጠቁ ህፃናት ህክምና የሚያገኙበት ሆስፒታል በኢትዮጵያ ሊያቋቁም እንደሆነ አስታወቀ። ሆስፒታሉ ከኢትዮጵያ በጉዲፈቻ ወስደው በሚያሳድጓት ዘሀራ ስም የሚሰየም ይሆናል።
በኢትዮጵያ የሚቋቋመው ሆስፒታል ፋውዴሽኑ በካምቦዲያ የመሰረተውንና ህፃናት ህክምና፣ ትምህርትና ማህበራዊ አገልግሎት የሚያገኙበትን ሆስፒታል ሞዴል እንደሚያደርግም ተገልጿል።
አንጀሊና ጆሊ ምስረታውን በተመለከተ በሰጠችው መግለጫ እንደተናገረችው ፋውዴሽኑ በኢትዮጵያ በሳምባ ነቀርሳና በ ኤች አይ ቪ ያለአግባብ ህይወታቸውን የሚያጡ ህፃናትን በመታደግ በካምቦዲያ ያገኘውን ስኬት በኢትዮጵያም የመድገም አላማ እንዳለው ተናግራለች።
ብራድ ፒት በበኩሉ ዘሃራ ኃላፊነት የምትሸከምበት እድሜ ላይ በደረሰች ጊዜ ሆስፒታሉን በማስተዳደር የተቋቋመለትን ተልዕኮ እንደምታስቀል ተስፋ እናደርጋለን ብሏል።