ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በየዓመቱ ጥር 11 ቀን የሚከበረው የጥምቀት በዓል የጋራ ግብር ኃይሉ ከኅብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ በመስራቱ ያለምንም የፀጥታ ስጋትና ችግር አዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማን ጨምሮ በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች በሰላም ተከብሮ መጠናቀቁን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብር ኃይል አስታውቋል።
የጋራ ግብርኃይል ከሃይማኖት አባቶች፣ ከደብር ኃላፊዎች፣ ወጣቶችና ሴቶች እንዲሁም ከበዓሉ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ጋር ተቀናጅቶ በመስራቱ በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም መጠናቀቁን ገልጿል።
ለበዓሉ ድምቀትና ስኬት መላው የሀገራችን ሕዝብ የበኩሉን አስተዋፅኦ በማበርከቱና የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይሉ ከማዕከል በሚሰጠው ትዕዛዝ ሥራውን በአግባቡ በመምራቱ እንዲሁም የፀጥታ ሥራውን ለማሳለጥ ቴክኖሎጂን በከፍተኛ ደረጃ በመጠቀም የፀጥታና የደኅንነት አካላት የመፈፀም አቅማቸው በከፍተኛ ደረጃ ያደገበት ሁኔታ በመፈጠሩ እንደሆነም ታውቋል።
በተጨማሪም የጋራ ግብርኃይሉ በቅንጅትና በጠንካራ አመራር ከማዕከል በሚሰጥ ትዕዛዝ በመመራት እንዲሁም ችግር ያጋጥማል ተብሎ የተጠረጠሩ ቦታዎችን አስቀድሞ ለይቶ በማሰማራት በዓሉን በስኬት ማጠናቀቅ ተችሏል ብሏል።
ለበዓሉ በሰላም መጠናቀቅ ሕዝበ ክርስቲያን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የደብር ኃላፊዎች፣ ወጣቶችና ሴቶች እንዲሁም በዓሉን ለማስተባበር በየደረጃው የተዋቀሩ ኮሚቴዎች ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ግብርኃይሉ ምስጋናውን አቅርቧል።
በተመሳሳይም የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብርኃይል ይህ ታላቅ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ሌት ተቀን በመስራት ኃላፊነታቸውን በብቃት ለተወጡት የግብርኃይሉ አባላት በሙሉ ምስጋናውን አቅርቧል።

























