በጋንቤላ ክልል በታጣቂዎች የ8 ሰዎች ህይወት አለፈ

በጋንቤላ ክልል በታጣቂዎች የ8 ሰዎች ህይወት አለፈ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በጋምቤላ ክልል ከደቡብ ሱዳን የሚነሱ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ድንበር አቋርጠው በመግባት ጥቃት ማድረሳቸውን የክልሉ ፖሊስ አስታወቀ።

በጥቃቱ የ8 ሠዎች ህይወት ሲያልፍ በ5 ሠዎች ላይ ደግሞ ከባድና ቀላል ጉዳት መድረሱን ተገልጿል። የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቡላ ኡቦንግ፥ በጋምቤላ በዚህ ሰዓት በጋ ስለሆነ እና ክልሉን ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚያጋራው ድንበር ሰፊና ክፍት ስለሆነ የታጣቂዎች የመግባትና የመውጣት አዝማሚያ አለ ብለዋል።

የሙርሌ ታጣቂዎች ትናትና ድንበር አቋርጠው በመግባት በኑዌር ዞን አኮቦ ወረዳ በካንካን ቀበሌ ድንገተኛ ተኩስ በመክፈት የ8 ሠዎች ህይወት ወዲያው ሲያልፍ 5 ሠዎች ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት መድረሱን አመልክተዋል።

ኮሚሽነር አቡላ አክለውም ክልሉ በአሁኑ ሰዓት ልዩ ኃይሉንና ሚሊሻ በመጠቀም ሰላምና ፀጥታ የማስከበር ስራውን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ኮሚሽነሩ፤ የአካባቢው ማህበረሰብ የታጣቂ ቡድኑን እንቅስቃሴ ነቅቶ በመጠበቅ ለመንግሥት ተገቢውን ጥቆማ ማድረግ እንደሚኖርበት አሳስበው በደረሰው ጉዳት ማዘናቸውን ገልጸዋል።

የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ከዓመታት በፊት፤ በኑዌር ዞን እና አኙዋ ዞኖች ገብተው በርካታ ሕፃናት አፍነው ሲወስዱ፣ ከአንድ መቶ ሰባ በላይ ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን ማጣታቸው ይታወሳል። ከ2 ሺህ በላይ ከብቶች መውሰዳቸውንም ኮሚሽነሩ አስታውሰዋል።

በወቅቱ የኢፌድሪ መከላከያ ሠራዊት ወደ ደቡብ ሱዳን በመግባትና ታጣቂዎቹ የሚኖሩበት አካባቢ ላይ ጥቃት በመፈፀም ታፍነው ከተወሰዱት ሕፃናት መካከል ከ100 ሕፃናት በላይ ወደ ቤተሰቦቻቸው መመለሱን አስረድተዋል።

LEAVE A REPLY