ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ማቋቋምያ አዋጅን ባለፈው ሳምንት መፈረማቸውን ነው በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት ያስታወቁት።
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን እንዲቋቋም መፈረም ኃላፊነቴ ቢሆንም የእውነተኛና አካታች ብሔራዊ ምክክርን ቁልፍነት ስለማውቅ፣ ስለሠራሁበት፣ ውጤቱንም ስላየሁ አምንበታለሁ ነውሲሉ ገልጸዋል፡፡
እንደዚህ ያለ ምክክር በመሠረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት እንዲኖር ያደርጋል፣ ሃሳብን በግድ መጫንን፣ ጦር መማዘዝን፣ ሕዝብንና አገርን አደጋ ላይ መጣልና ከመሳሰሉ አደጋዎች ያድናል ሲሉ ነው የገለጹት፡፡
የንግግር፣ የመደማመጥ የመከባበር አዲስ ባህል ይፈጥራል፣ እንደ እኛ ከአውዳሚ ጦርነት ማግስት ለሚገኝ አገር ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።
ይህንን አገራዊ ምክክር እንዲመራና እንዲያካሂድ የሚቋቋመው ኮሚሽን አባላት ጥቆማ ሲካሄድ መቆየቱን በማንሳት፥ ለአንድ ሳምንት ከተራዘመ በኋላ ዛሬ ጥር 13 ቀን 2014 እንደሚያበቃም ጠቁመዋል።
ለኮሚሽነርነት የተጠቆሙ ሴቶች ቁጥር አነስተኛ ይሆናል ብዬ እሰጋለሁ፣ ሴቶች መጠቆም አለባቸው፣ አሸባሪው ህወሓት የከፈተው ጦርነት በሴቶች ላይ ያደረሰው ሰቆቃ ከፍተኛ ነው ብለዋል።