ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በአዲስ አበባ የሚካሄደው 35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ኢትዮጵያ ፈተናዎቿን በድል ተሻግራ በቁርጥ ቀን ልጆቿ ችግሯን በራሷ ፈታ ወደፊት የቀጠለች መሆኑን የምናሳይበት መሆኑን የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ገለፀ።
የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ዛሬ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዳይካሄድ ብዙ ቅስቀሳ እንደነበር አንስተው፥ ሆኖም የጉባኤው ተሳታፊዎች የትኛውንም ጫና ተቋቁመው ለህብረቱ መርሆች ተገዢ ሆነው በህብረቱ መቀመጫ መደበኛ ባህሪዉን ጠብቆ እንዲካሄድ መወሰናቸው ያስመሰግናቸዋል ነው ያሉት ሚኒስትሩ ፡፡
በዚህም ውሳኔያቸው ለኢትዮጵያ ያላቸውን አጋርነት አሳይተዋል ያሉት ሚኒስትሩ፥ ይህም ተግባራቸው የሚያስመሰግናቸው ነው ብለዋል።
በመሆኑም መላው ህብረተሰብ በተለይ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንዲሁም የአገልግሎት ሰጪተቋማት ተሳታፊዎች ደህንነት እንዲሰማቸው ባህላችንን የጠበቀ የእንግዳ አቀባበል ስርዓት ማሳየት እንደሚገባ መንግስት ጥሪ ያቀርባል ብለዋል፡፡