በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ የተመራ ልዑካን ቡድን በሳዑዲ አረቢያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት...

በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ የተመራ ልዑካን ቡድን በሳዑዲ አረቢያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አደረገ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ቡድኑ ባለፉት አራት ቀናት በነበረው ቆይታ በሪያድ ከኢትዮጵያ ኮሙኒቲ አመራሮች እና አባላት፣ ከሀይማኖት መሪዎች እንዲሁም የንግዱ ማህበረሰብ ጋር የተወያየ ሲሆን፣ ከሳዑዲ መንግስት በኩል ከአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል አብዱል አዚዝ ቢን ሳዑድ ቢን ናየፍ፣ ከሳዉዲ ሮያል ፍርድ ቤት አማካሪ እና የንጉስ ሰልማን የሰብዓዊ እርዳታ ማዕከል የበላይ ተቆጣጣሪ ከሆኑት ከዶ/ር ቢን አብዱልአዚዝ አል ራቢህ ጋር መወያየቱ ተገልጿል፡፡

በውይይቱ ወቅትም እስር ቤት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አያያዝ ስለሚሻሻልባቸው፣ የመኖሪያ ፈቃዳቸው የተቃጠለና የተለያዩ ቅጣቶች የሚጠብቋቸው ነገር ግን በራሳቸው ገንዘብ ተሳፍረው አገራቸው መግባት ለሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ቅጣት ተነስቶላቸውና ምህረት ተደርጎላቸው ወደ አገራቸው መመለስ በሚችሉባቸው አግባቦች ተወያይተዋል፡፡

እንዲሁም ፈቃድ እያላቸው የተለያየ ወከባ ይደርስብናል የሚል ስጋት ያላቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን መኖራቸው ስለሚሰማ ይኸው ሁኔታ ስለሚሻሻልበት፣ እስር ቤት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በተቻለ ፍጥነት ዝግጅት ተደርጎ ወደ አገራቸው በሚመለሱበት እና ይህንን ችግር በመፍታት የሁለቱን አገሮች ስትራቴጂካዊ ትብብርና ግንኙነት ወደላቀ አጋርነት ማሸጋገር በሚቻልባቸው አግባቦች ዙሪያ ከፍተኛ ልዑካን ቡድኑ ተወያይቷል መባሉን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡

LEAVE A REPLY