ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የቀድሞው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ታስረው ችሎት እንዲቀርቡ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ትዛዝ ሰጠ።
ከህዳር 4 ቀን 2011 ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞ የሜቴክ ዳሪክተር ሜ/ጀነራል ክንፈ ዳኘውን ጨምሮ አራት ተከሳሾች ከዕርሻ መሳሪያ ግዢ ጋር ተያይዞ በተመሰረተባቸው የሙስና ክስ የመከላከያ ማስረጃ ማሰማት መጀመራቸው ይታወሳል።
በዚህም መሰረት በሀምሌ 11ቀን 2013 የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ፍርድ ቤት ቀርበው እ.ኤ. አ በ2014 በተደረገ በዝቅተኛ ወለድ ስምምነት ኢትዮጲያ ከፖላንድ መንግስት ባገኘችው 50 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ እዛው ፖላንድ አገር ለሚገኙ የዕርሻ መሳሪያ መለዋወጪያ ኩባንያዎች መከፈሉን እና ገንዘቡ ወደ አገር ውስጥ አለመምጣቱን በማብራራት የመከላከያ የምስክርነት ቃላቸው ተሰምቶ ነበር።
ሌላው በዚሁ የክስ መዝገብ በመከላከያ ምስክርነት እይዲቀርቡ በተደጋጋሚ መጥሪያ እንዲደርሳቸው ትዛዝ ተሰቶባቸው የነበሩት ሀይለማርያም ደሳለኝ ናቸው።
ሀይለማርያም ደሳለኝ መጥሪያ እንዲያደርስ የታዘዘው የፌደራል ፖሊስ በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በኩል አፈላልጌ ላገኛቸው አልቻልኩም ሲል መልስ ሰቶ ነበር።
የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው ሀይለማርያም ደሳለኝ በግላቸው የሮማን ፉውንድሽን እንደሚሰሩና በመንግስ ፖሊስ እጀባ እየተደረገላቸው እንደሚቀሳቀሱ ጠቅሰው፣ ይህ በሆነበት ሁኔታ ፖሊስ ላገኛቸው አልቻልኩም በማለት የሰጠው ምላሽ አግባብነት የሌለው ነው ሲሉ በድጋሚ ትዛዝ እንዲሰጥላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ፖሊስ ሀይለማርያምን ደሳለኝን ካሉበት አፈላልጎ አስሮ እንዲያቀርባቸው ትዛዝ ሰቷል። በዚሁ መዝገብ የተከሳሾችን የመከላከያ ማስረጃ ለመስማት ለመጋቢት 8፣ 9 እና 12 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰቷል።