ግማሽ ሚልዮን ብር በሙስና ሲቀበል የተያዘው ግለሰብ በፅኑ እስራት ተቀጣ

ግማሽ ሚልዮን ብር በሙስና ሲቀበል የተያዘው ግለሰብ በፅኑ እስራት ተቀጣ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በገቢዎች ሚንስቴር ውስጥ የኦዲት ባለሙያ ሆኖ ሲሰራ 1.5 ሚሊየን ብር ጉቦ ለመቀበል ተስማምቶ ግማሽ ሚሊየን ብር በጥሬ ገንዘብ ሲቀበል እጅ ከፍንጅ የተያዘው ተከሳሽ በፅኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጣ።

መላኩ ሸዋረጋ የተባለው ተከሳሽ በገቢዎች ሚንስቴር አዳማ ቅ/ፅ/ቤት የኦዲት ባለሙያ ሆኖ ሲሰራ አንድ ሚሊየን ብር በባንክ አካውንት እንዲገባለትና 5 መቶ ሺህ ብር ደግሞ በጥሬው ለመቀበል ተስማምቶ በቦሌ ክፍለ ከተማ ካፒታል ሆቴል ገንዘብ ሲቀበል የተገኘው ተከሳሽ በፈፀመው ጉቦ መቀበል የሙስና ወንጀል በፅኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጣ ተወስኖበታል።

ተከሳሹ የተጣለበትን የስራ ኃላፊነቱን ተጠቅሞ ኽርበርግ ሮዝ ኃ/የተ/የግ/ማህበር የተባለው ድርጅት የ2 ዓመት የንግድ ስራ ትርፍ ግብር ብር 66‚616‚818 ብር ከ93 ሳንቲም አንዲከፍል ሲወሰንበት የድርጅቱ የአስተዳደር ሰራተኛ የሆነችው 1ኛ የዐቃቤ ህግ ምስክር በውሳኔው ላይ ለቅ/ፅ/ቤቱ ቅሬታ ታቀርባለች፡፡

ተከሳሹ በበኩሉ የቀረበውን ቅሬታ ውሳኔውን ዝቅተኛ በሆነ መልኩ መወሰን እንደሚቻልና ለዚህም ብር 1‚000‚000 ብር በባንክ ለመቀበልና ቀሪውን 500‚000 ብር ደግሞ እጅ በእጅ ለመቀበል ከተደራደረና ከተስማማ በኋላ ጥቅምት 24/3013 ዓ.ም ከቀኑ 8:30 ሰዓት ሲሆን በቦሌ ክፍለ ከተማ ካፒታል ሆቴል ውስጥ 500‚000 ብሩን ሲቀበል እጅ ከፍንጅ ተይዟል።

በፈፀመው ጉቦ መቀበል የሙስና ወንጀል በፍትሕ ሚኒስቴር ክስ መስርቶበታል።
በከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ በአንደኛ የሙስና ወንጀል ችሎት የቀረበው ተከሳሽ መላኩ ሸዋረጋ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎበት በ4 ዓመት ከ10 ወር ፅኑ እሥራት እና በ2500 ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ተወስኗል።

እንዲሁም በጉቦ የተሰጠው ገንዘብ ለተበዳይ እንዲመለስ ዐቃቤ ህግ በጠየቀው መሰረት ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ገንዘቡ ለተበዳይ እንዲመለስ ተደርጓል፡፡

LEAVE A REPLY