ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ህወሃት አዲስ ጦርነት በከፈተበት በአፋር ክልል ኪልበቲ ረሱ ዞን የሚገኙ ስድስት ወረዳዎችን መቆጣጠሩና በነዚህ ወረዳዎችም ከ300 ሺህ በላይ ንፁሃን አርብቶ አደሮች መፈናቀላቸዉን የአፋር ክልል ፕሬዝዳንት አወል አርባ መግለጻቸዉን የክልሉ ኮሙኒኬሽን አስታወቀ።
አቶ አወል አርባ ይሄን ያሉት በፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴና በተመድ ምክትል ዋና ፀሀፊ አሚና መሀመድ ከተመራው ልኡክ ጋር በተወያዩበት ወቅት ህወሀት በአፋር ህዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን የዘር ማጥፋት የጅምላ ግድያ ግፍና ሰቆቃ አስመልክቶ ለልኡኩ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት መሆኑ ተገልጿል።
በእነዚህ አካባቢዎች ህፃናት፣ ሴቶችና አዛውንቶች ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ የዘር ማጥፋት የፈፀመ እንደሚገኝ እና ዜጎች ከባድ ለሆነ ስቃይና እንግልት መዳረጋቸውን የገለጹት ፕሬዝዳንት አወል አርባ በከበደ ችግር ውስጥ ላለው የአፋር ህዝብ አስቸኳይ የሰብአዊ ድገፍ እንዲደረግ ጥሪ ማቅረባቸውም ተሰምቷል።
ፕሬዝዳንቱ በማብራሪያቸው አሸባሪው ህወሀት ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ በአፋር ንፁሀን አርብቶ አደሮች ላይ እያደረሰ ያለው የዘር ማጥፋት እንዳልቆመና አርብቶ አደሩ ህዝብን ከጅምላ ግድያ የዘር ማጥፋት ጀምሮ ስቃይ እና እንግልት እያደረሰ መሆኑን ገልፀዋል ነዉ የተባለዉ።
ፕሬዝዳንቷ አለም የገዳዮችን ድምፅ የሚሰማበት የሟቾችን ድምፅ የማይሰማበት ምክንያት ምን ይሆን?” ሲሉ በመጠየቅ የአለም መንግስታትና ሚዲያዎች የሟቾችን ድምፅ ሊሰሙ ይገባል ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል።
ከውይይቱ በኋላም ልኡካን ቡድኑ አሸባሪዉ ህወሀት በቅርቡ በኪልበቲ ረሱ ዞን በከፈተው ጦርነት በከባድ መሳሪያ ባደረገው ድብደባ የተጎዱ ህፃናትን በዱብቲ ሆስፒታል በመገኘት የጎበኙ ሲሆን በጉብኝታቸው ባዩት ነገር በጣም ማዘናቸውንና ችግሩ መፍትሄ እንዲያገኝ እንደሚሰሩም መገለጹን ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።