ኢትዮጵያ ነገ ዜና || አዲሱ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድ አዲስ አበባ እንደሚገኙ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አስታውቋል።
የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር በቀድሞው የአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጀፍሪ ፊልትማን ምትክ በቱርክ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩትን ዴቪድ ሳተርፊልድን ለቀጠናው ልዩ መልዕክተኛው አድርጎ ባሳለፍነው ወር መጀመሪያ ላይ መሾሙ ይታወሳል።
አዲሱ የቀጠናው ልዩ መልዕክተኛ ዴቪድ ሳተርፊልድ ትናንት የካቲት 06/2014 አዲስ አበባ መግባታቸውን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ያስታወቀ ሲሆን በኢትዮጵያ በሚኖራቸው የሁለት ቀናት ቆይታ፤ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ከአፍሪካ ሕብረት እና ከተባበሩት መንግሥታት ተወካዮች እና ከሰብዓዊ ድርጅት አስተባባሪዎች ጋር በአዲስ አበባ እንደሚገናኙም ገልጿል።
በአዲስ አበባ በሚኖራቸው ቆይታም በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው ጦርነት በሰላም በሚፈታበት ሁኔታ ላይ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር እንደሚመክሩ ይጠበቃል።
ዴቪድ ሳተርፊልድ በቱርክ፣ በሶሪያ፣ በቱኒዚያ፣ በሳዑዲ አረቢያ እና ሊባኖስ ውስጥ አገራቸውን ወክለው በዲፕሎማትነት የሰሩ ሲሆን፤ በመካከለኛው ምሥራቅ ዲፕሎማሲ ዙሪያ ለአራት አስርተ ዓመታት ያህል ልምድ ያካበቱ መሆናቸው ይነገርላቸዋል።
አምባሳደሩ በቱርክ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ከመሾማቸው በፊት በዶናልድ ትራምፕ የሥልጣን ዘመን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ የነበሩት ማይክ ፖምፔዮ ከፍተኛ አማካሪም ሆነውም አገልግለዋል።