ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠዉ

ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠዉ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ላለፉት 70 ቀናት በኦሮሚያ ክልል ገላን ከተማ በእስር ላይ የነበረው የተራራ ኔትዎርክ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ በዛሬዉ ዕለት ፍርድ ቤት ቀርቦ ለየካቲት 17 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቶታል።

ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ይስጠኝ ሲል ጠይቆ የነበረ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ የ 7ቀን የጊዜ ቀጠሮ ፈቅዶለት ለየካቲት 17 /2014 ተለዋጭ ቀጠሮ እንደሰጠ ተገልጿል፡፡

ጋዜጠኛ ታምራት በኦሮሚያ ልዩ ዞን የገላን ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ባለፈዉ ታህሳስ 21/2014 የቀረበ ቢሆንም ፖሊስ “ምርመራዬን አጠናቅቂያለሁ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ አያስፈልገኝም የምርመራ መዝገቡም ይዘጋ ሲል ፍርድ ቤቱን በመጠየቁ የገላን ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት የምርመራ መዝገቡን ዘግቶ ጉዳዩም ወደ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲተላለፍ መወሰኑ የሚታወስ ነው።

የህዝብ ተወካዮች መክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ባለፈዉ ማክሰኞ ማንሳቱ የሚታወስ ሲሆን፤ ይሁን እንጅ ፖሊስ ጉዳዩን ዳግም ወደ መደበኛዉ የምርመራ መዝገብ እንደወሰደዉ ታዉቋል፡፡

የአቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተነሳ በ48 ሰዓታት ዉስጥ ከእስር የማይለቀቅ ከሆነ ወደ ፍርድ መቅርብ እንዳለበት ህጉ የሚደነግግ በመሆኑ በዛሬዉ ዕለት ከጠዋቱ 5 ሰዓት ገደማ በኦሮሚያ ልዩ ዞን ገላን ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ቀርቦ ፖሊስ ለተጨማሪ ምርመራ 7 ቀን ተፈቅዶለታል።

ጋዜጠኛ ታምራት የዋስትና መብቴ ይጠበቅልኝ ሲል ቢጠይቅም በቀጣይ ቀጠሮ መጠየቅ ትችላለህ የሚል መልስ እንደተሰጠዉም ቤተሰቦቹ ተናግረዋል ሲል ተራራ ኔትዎርክ ዘግቧል፡፡

LEAVE A REPLY